ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ኔይማርና ሌሎች ተጫዋቾች ስለ ታላቁ እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ምን አሉ?
ከፔሌ በፊት እግር ኳስ ስፖርት ብቻ ነበረ፤ ፔሌ ሁሉን ነገር ቀይሯል- ኔይማር
ፔሌ ለእግር ኳስ የትናንት፣ የዛሬ እንዲሁም የዘላለም ማሳያ ነው”- ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ ትናንተ ምሽት በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ በካንሰር ህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ሲከታተል የቆየ ሲሆን፤ ትናንት ምሽት የህልፈቱ ዜና ተሰምቷል።
የህልፈቱን ዜና ተከትሎም የዓለማችን ሀገራት መሪዎች፣ እውቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
ብራዚላዊው ኮከብ ተጫዋች ኔይማር ጁኒየር ከፔሌ በፊት እግር ኳስ ስፖርት ብቻ ነበር፤ ፔሌ እግር ኳስን ወደ ጥበብ እና መዝናኛነት መቀየር የቻለ ተጫዋች ነው ብሏል።
ፔሌ ለእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን፤ ለደሃዎች እና ለጥቁሮች ድምጽ መሆን የቻለ በዋናነትም ብራዚል ደምቃ እንድትታይ ማድረግ የቻለ መሆኑን ኔይማር አስታውቋል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶም “ፔሌ ሚሊየኖችን ማነሳሳት የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር፤ ፔሌ ለእግር ኳስ የትናንት፣ የዛሬ እንዲሁም የዘላለም ማሳያ ነው” ያለ ሲሆን፤ ለወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹ መጽናናትን ተመኝቷል።
የፈረንሳዩ ኮከብ ኪሊያን ምባፔም፤ የእግር ኳስ ንጉስ ተለይቶናል፤ ነገር ግን ፔሌ ለእግር ኳስ ያበረከተው መቼም አይረሳም ብሏል።
አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲም በፔሌ ህልፈት ሀዘኑን የገለፀ ሲሆን፤ ከፔሌ ጋር የተነሱትን ፎቶ ግራፍ በትዊተር ማህበራዊ ገጽ ላይ በማጋራት ሀዘኑን ገጿል።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር፣ የእንግሊዝ ፐሪምየር ሊግ እና ሌሎችም የእግር ኳስ ስፖርት ማህበራትም የፔሌን ታላቅነት በመግለጽ በህልፈቱ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ በ 1940 የተወለደው ፔሌ እግር ኳስ ገና በልጅነቱ በአስራ አምስት ዓመቱ በሳንቶስ ክለብ በመጫወት መጀመሩ ይታወቃል።
በአራት የዓለም ዋጫዎች ላይ መጫወት የቻለው ፔሌ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር ሶሰት የዓለም ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል።
ፔሌ በሳንቶስ ቆይታውም ከክለቡ ጋር ስድስት የሊግ ዋንጫ ፣ ሁለት ኮፓ ሊቤርታዶሬስ እና ሁለት ኢንተር ኮንቲኔንታል ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካለ ፊፋ ፔሌን ታላቁ ተጫዋች ሲል የሚጠራው ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2000 የአለም አቀፍ እግር ኳስ እና ታሪክ የምትዓመቱ የዓለማችን ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን መቀዳጀቱም ይታወቃል።
ፔሌ በእግር ኳ ዘመኑ 1 ሺህ 228 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 77ቱ ለሀገሩ ብራዚል ያስቆጠራቸው ናቸው።