“ገንዘብ ለመቆጠብ” በቅንጡ ሆቴል መኖር የጀመሩት ቻይናውያን
ቤት ከመከራየትም ሆነ ገዝቶ ከመኖር ይልቅ በሆቴል መኖር ይሻላል በሚል በቅንጡ ሆቴል መኖር ከጀመሩ 229 ቀናት ተቆጥረዋል
ቻይናውያኑ በሆቴል መኖር የመብራት፣ ውሃ፣ መኪና ማቆሚያና ሌሎች ወጪዎችን አስቀርቶልናል ይላሉ
በቻይና ወጪ ለመቀነስ በሚል በቅንጡ ሆቴል መኖር የጀመሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።
በሄናን ግዛት ናንያንግ በተባለችው ከተማ ነዋሪ የሆኑት ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላት በቅንጡ ሆቴል መኖር ከጀመሩ 229 ቀናት ሆኗቸዋል።
ለአንድ ምሽት 1 ሺህ ዩዋን ወይም 140 ዶላር የሚያስከፍል ባለሁለት መኝታ ቅንጡ ማረፊያ ውስጥ መኖር የጀመሩት ቻይናውያኑ ቤተሰቦች ከዚህ ሆቴል መውጣት አንፈግም ማለታቸው ነው አነጋጋሪ የሆነው።
“በሆቴሉ ውስጥ መኖር ከጀመርን በኋላ ደስተኞች ነን፤ ስምንታችንም በጥሩ ሁኔታ እየኖርን ነው፤ እንዲህ አይነቱ አኗኗር በዚህ ደረጃ ወጪያችን ይቀንሳል ብዬ አስቤ አላውቅም” ብሏል ሙ ሹይ የተባለው የቤተሰቡ አባል።
ለበርካቶች እጅግ ውድ የሆነው ክፍያ ስምንት አባላት ላሉት ቤተሰብ አዋጭ ተደርጎ የታሰበው በርካታ ወጪዎችን ስላስቀረ ነው።
በቅንጡ ሆቴሉ ውስጥ መኖር ቤት ተከራይቶ አልያም ገዝቶ በመኖር ሂደት ውስጥ የሚኖሩ የመብራት፣ ውሃ፣ መኪና ማቆሚያ እና ሌሎች ወጪዎችን ማስቀረቱንም በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
የሙ ሹይ ቤተሰብ ከናንያንጉ ቅንጡ ሆቴል መውጣት እንደማይፈልግም ነው የተገለጸው።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች መከራከሪያ ሆኗል።
በየቀኑ 140 ዶላር መክፈል የሚችሉ ሰዎች እንዴት ቤት መከራየት ሊከብዳቸው ይችላል፤ በባለሁለት መኝታው ክፍል ውስጥ እንዴት ስምንት ሰዎች መኖር ቻሉ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን ከመሻት ያለፈ ምክንያት አይኖራቸውም የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
ስታር የተባለ የማህበራዊ ትስስር ገጽም የሹይ ቤተሰቦች የፋይናንስ አቅማቸው የደረጀ ስድስት ቤቶችም ያሉት መሆኑን የሚያሳዩ ሰነዶችን አውጥቷል።
ቻይናውያኑ ከ200 ቀናት በላይ በሆቴሉ ለመቆየትም ለቅንጡ ሆቴሉ በባንክ ውስጥ በመቶ ሺህ ዩዋን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳላቸው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማቅረባቸውን ይፋ አድርጓል።
ሃብት እያላቸው “ወጪ ለመቀነስ” ቅንጡ ሆቴል ውስጥ መኖርን መርጠናል ማለታቸውም በኑሮ ውድነት በሚንገላቱ ቻይናውያን ላይ እንደመሳለቅ ይቆጠራል የሚሉ ትችቶች በስፋት እየተነሳባቸው ነው።