ፔፕ ጋርዲዮላ ለማንችስተር ሲቲ አቋም መውረድ ተጠያቂ መሆናቸውን ተናገሩ
አሰልጣኙ “ቡድኑ ከሚገኝበት የውጤት ቀውስ እንዲወጣ የሚጠበቅብኝን አላደረኩም” ብለዋል
ከመሪው ሊቨርፑል በ14 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ6ተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝው ሲቲ ዛሬ ምሽት 12 ሰአት ዌስትሀምን ይገጥማል
የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድኑ ለሚገኝበት የውጤት ማጣት ተጠያቂ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ላለፉት አራት አመታት ያሸነፈው ሲቲ በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው ሊቨርፑል በ14 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል።
ለክለቡ አስከፊ የውድድር ዘመን ተጠያቂ ነኝ ያሉት ስፔናዊው አሰልጣኝ “ማድረግ ሲኖርብኝ ያላደረኩት አንድ ነገር እንዳለ ይሰማኛል” ብለዋል
ያለፉት አራት አመታት የፕርሚየርሊጉ ሻምፒዮን የነበረው ሲቲ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባለፈው እሁድ ሌስተር ሲቲን 2-0 ያሸነፉበት ጨዋታ በ14 ጨዋታዎች ሁለተኛ ድሉ ነበር።
ጋርዲዮላ በባርሴሎና እና በባየርሙኒክ ካሳለፉት ስኬታማ የአሰልጣኝነት ጊዜ በኋላ በዘመናቸው አስከፊውን ጊዜ እያሳለፉ እንደሚገኙ የእንግሊዝ ጋዜጦች ጽፈዋል፡
በክለቡ ለዘጠኝ የውድድር ዘመን የቆዩት “አሰልጣኙ ጥሩ እየሰራሁ አይደለም ብዙ ጨዋታዎችን ስትሸነፍ ለአሰልጣኙ ከባድ ሀላፊነት ነው በዚህ ጊዜ ቡድኑ የሚፈልገው በራስ መተማመንን ነው ነገር ግን እኔ ይህን ማድረግ አልቻልኩም” ነው ያሉት።
የእንግሊዙ ክለብ ከዚህ ቀደም በነበሩ የውድድር ዘመኖች አዝጋሚ አጀማመር ሲያሳይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ፡፡
ነገር ግን ባለፉት አራት ዋንጫ በበላባቸው የውድድር አመታት መሪዎቹን በስድስት ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ነጥብ ይከተላል እንጂ እንደዚህ ውጤት ርቆት አያውቅም ።
በቡድናቸው ውጤት መዋዤቅ ደስተኛ ያልሆኑት ስፔናዊው አሰልጣኝ ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት ክለቡ አሁን ባለበት አቋም የሚቀጥል ከሆነ በገዛ ፈቃዳቸው ከሀላፊነት እንደሚነሱ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም ማንችስተር ሲቲ የመጨረሻ የሚያሰለጥኑት ቡድን ሊሆን እንደሚችል ጋርዲዮላ ተናግረዋል፡፡
ከመሪው ሊቨርፑል በ14 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ6ተኛ ደረጃ ለይ የሚገኝው ሲቲ ዛሬ ምሽት 12 ሰአት ላይ ከዌስትሀም ጋር ግጥሚያውን ያደርጋል፡፡
በነገው ዕለት መሪው ሊቨርፑል በተመሳሳይ የውጤት ማጣት ላይ ከሚገኝው ማንችስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡