የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ጋርዲዮላ ቡድኑ በሚገኝበት የውጤት ማጣት የሚቀጥል ከሆነ ከሀላፊነት እንደሚለቁ ተናገሩ
ሲቲ በነገው እለት ፕሪምየርሊጉን ከሚመራው ሊቨርፑል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ የነጥብ ልዩነቱ ወደ 11 ከፍ ይላል
በ32 የውድድር ዘመናት ከ11 ነጥብ ልዩነት ተነስተው ሊጉን ማሸነፍ የቻሉት 3 ቡድኖች ብቻ ናቸው
የማንቺስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድኑ በሚገኝበት የውጤት ማጣት የሚዘልቅ ከሆነ ከሀላፊነታቸው እንደሚለቁ ተናገሩ።
ሲቲ ካለፉት 6 ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱን መሸነፉን ተከትሎ ጋርዲዮላ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ረጅሙን የሽንፈት ጉዞ እንዲያሳልፉ ተገደዋል።
ባለፈው ሳምንት አዲስ የውል ማራዘሚያ ኮንትራት የፈረሙት ጋርዲዮላ ከተጠያቂነት መሸሽ አልፈልግም ማንም ላይ ጣቴን አልቀስርም ነገር ግን እንደአሰልጣኝ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ካልቻልክ ችግር ውስጥ እንደምትገባ አውቃለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኙ አክለውም ለቡድኑ ትክክለኛው ሰው እንዳልሆኑ ባመኑበት ቅጽበት ከሃላፊነታቸው ራሳቸውን እንደሚያነሱ ነው የገለጹት።
"ሰዎች በእኔ ይተማመናሉ እንደ ማንችስተር ሲቲ አይነት ትላልቅ ክለቦች አሁን የምንገኝበትን የውጤት ማጣት ሁኔታ መመልከት የተለመደ አይደለም፤ ቡድኑን ለማሻሻል እና የውጤት ቀውሱን ለመቀልበስ እሰራለሁ ይህን ማሳካት ካልቻልኩ ግን ከቡድኑ ጋር የሚኖረኝ ቆይታ የሚጠናቀቅ ይሆናል ነው ያሉት።
በሚቀሩት ጊዜያት ቡድኑን ለማዋቀር አዳዲስ ዘዴዎችን ለመከትል እንደሚጥሩ የተናገሩት አሰልጣኙ ከቡድኑ ስለሚልቁበት ሁኔታ ከመናገራቸው ውጪ የጊዜ ቀነ ቀደብ አላስቀመጡም።
ነገር ግን በንግግራቸው የውድድር ዘመኑን መጠናቀቂያ እና የሚቀጥለውን የውድድር አመት አዳዲስ መንገዶችን ለመሞከር እንዳሰቡ ገልጸዋል።
ማንችስተር ሲቲ በነገው ዕለት ፕሪምየርሊጉን በ8 ነጥብ እየመራ ከሚገኝው ሊቨርፑል ጋር ወሳኝ የተባለውን ጨዋታ ያደርጋል።
በሊጉ ጨዋታዎችን ካሸነፉ 34 ቀናትን ያስቆጠረው ሲቲ በነገው ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱ ወደ 11 ከፍ የሚል ይሆናል።
ከዚህ ቀደም በ32 የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የውድድር ዘመናት ከ11 የነጥብ ልዩነት ተነስተው የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ የቻሉት 3 ቡድኖች ናቸው።
ከ11 ነጥብ ልዩነት ተነስቶ ሊጉን የማሸነፍ ታሪክ የሌለው ሲቲ በነገው የአንፊልድ ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ የሻምፒዮናነት እድሉ የሚያበቃለት ይሆናል።
ነገር ግን በ6 የውድድር አመቶች ከ8-10 የነጥብ ልዩነቶች በመነሳት ዋንጫን ማንሳት ችሏል፤ እናም የነገውን ጨዋታ አቻ የሚለያይ ከሆነ የዋንጫ ጉዞውን በጠባብ እድል ማስቀጠል ይችላል።
የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል የውጤት ልዩነቱን ለማስፋት ቼልሲ ፣ አርሰናል እና ብራይተን ነጥብ እንዲጥሉለት ይፈልጋል።
ዛሬ ምሽት 2 ሰአት የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በለንደን ስታድየም ዌስትሀምን ይገጥማማል ፣ በነገው እለት 10 ሰአት ደግሞ ዩናይትድ በኦልትራፎርድ ኤፈርተንን ያስተናግዳል በተመሳሳይ ሰአት ቼልሲ ከ አስቶንቪላ ይጫወታሉ።