የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ኮንትራቱን ሊያራዝም ነው
የእንግሊዝ ፕርሚየርሊግ ሻምፒዮናው ቡድን አሰልጣኝ እስከ 2026 የሚያቆየውን ውል ነው የሚያራዝመው
ባለፈው ወር የቡድኑ ደጋፊዎች አሰልጣኙ እንዲቆይ የሚጠይቁ ጽሁፎችን ይዘው ተስተውለዋል
ፔፕ ጋርዲዮላ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እስከ 2026 ድረስ ለመቆየት የሚያስችለውን የአንድ አመት ኮንትራት ሊፈራረም ነው።
ጋርዲዮላ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ኮንትራቱን መጨረሱን ተከትሎ በግንቦት ወር አራተኛ ተከታታይ የሊግ ዋንጫን ካነሳ በኋላ በቡድኑ ውስጥ የሚኖረው እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር።
አሰልጣኙ ለአንድ አመት የሚፈርመው ኮንትራት እስከ 2027 የውድድር ዘመን ድረስ የውል ማራዘሚያ እንደሚኖረው ተሰምቷል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ከሃላፊነት መልቀቁን ተከትሎ የ53 አመቱ አሰልጣኝ ጋርዴዮላ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥን ጥያቄ ቀርቦለት ነበር።
ባለፈው ወር አሰልጣኙ በቡድኑ አሰልጣኝነት እንዲቆይ የሚጠይቁ ባነሮች ቡድኑ ጨዋታ በሚያደርግባቸው ግጥሚያዎች ላይ ሲውለበለቡ ተስተውለዋል።
አዲሱን የአንድ አመት የውል ማራዘሚያ ተከትሎ በ2016 ሲቲን የተቀላቀለው ስፔናዊ አሰልጣኝ ቡቡድኑ የሚኖረው አጠቃላይ ቆይታ 10 አመት የሚሆን ይሆናል።
በቆይታውም ከማንችስተር ሲቲ ጋር ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ ሁለት ኤፍኤ ካፕ፣ አራት የሊግ ዋንጫዎችን እና የክለቡን የመጀመሪያ ሻምፒዮንስ ሊግ ማሸነፍ ችሏል።
በጋርዲዮላ የአሰልጣኝነት ዘመን ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝው የእንግሊዙ ቡድን ባለፈው አመት አራት ተከታታይ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በማሸነፍ የመጀመሪያው የወንዶች ቡድን ሲሆን፤ በአንድ የውድድር ዘመን 100 የፕሪምየር ሊግ ነጥብ ያስመዘገበ ብቸኛው ቡድን ነው።
ሲቲ በአሁኑ ሰአት ከመሪው ሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በሁሉም ውድድሮች በአራት ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።
በጋርዲዮላ በአሰልጣኝነት ጊዜም መሰል ሽንፈት ሲደርስበት ይህ የመጀመሪያው ነው።