በቡጢ ፍልሚያ ቅራኔዎችን የምትፈታው የፔሩ መንደር
ቹምቢቪልካስ በተባለችው ግዛት የገና በዓልን የሚያደምቀው ስነስርአት፥ ከማዝናናት ባሻገር እንደ ባህላዊ ፍትህ ማስፈኛም ይወሰዳል
የቤተሰብ፣ የፍቅር አልያም የይዞታ ይገባኛል ክርክርና ቅራኔ ያላቸው ሰዎች በቡጢ ተነራርተው የሚታረቁበት ፍልሚያ በየአመቱ ይጠበቃል
በፔሩ ደቡባዊ ክፍል የምትገኘው የቹምቢቪልካስ መንደር የገና በዓልን የሚያደምቅ ባህል አላት።
ዘመናትን የተሻገረ፣ የሚያዝናና ትርኢት ግን ደግሞ ሰዎችን ሊጎዳ የሚችል የቡጢ ፍልሚያ የሚስተናገድበት ትውፊታዊ የግጭት አፈታት ባህል።
አዲሱን አመት በይቅርታና ፍቅር ለመጀመር በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንደሯ ነዋሪዎች በሰፊ ሜዳ ላይ የሚደረገውን የቡጢ ፍልሚያ ለመመልከት ጓጉተው ይጠብቃሉ።
የአካባቢው ሰዎች “ታካናኩይ” እያሉ የሚጠሩት ይሄው ፍልሚያ ከቤተሰብ፣ ከፍቅር አልያም ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ቅራኔዎች ለቀጣዩ አመት እንዳይሸጋገሩ የሚደረግበት ባህላዊ የፍትህ ስርአት ነው።
ፍትህ በቡጢ እንዴት ይሰፍናል? ለሚለው ጥያቄውም ምላሽ አላቸው።
የቹምቢቪልካስ መንደር ነዋሪዎች ከሰሞኑ የገና በዓል ሲከበር አመታዊውን “የእርቅ ቡጢ” ፍልሚያ ለመመልከት ተሰባስበዋል፤ እየዘፈኑና እየተወዛወዙም ለሚደግፉት ወገን ብርታት ሲሰጡ ይታያል።
በዚህ አመቱ ውድድር 40 ሰዎች ለሁለት ደቂቃ የቡጢ ፍልሚያውን አድርገዋል ብሏል ውድድሩን በቀጥታ ያስተላለፈው ላ ሪፕብሊካ የተሰኘው የቴለቪዥን ጣቢያ።
የቡጢ ግጥሚያው ሃይል የበዛበትና ለክፉ የሚሰጥ እንዲሆን አይፈቀድም፤ አንደኛው ተፋላሚ ከደማ አልያም ወድቆ መከላከል የማይችል ከሆነ ወዲያውኑ ፍልሚያው ይቆማል።
ውድድሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ የሚካሄዱ ስነስርአቶች የፌስቲቫል መልክ ያላቸው ናቸው።
የምግብና መጠጥ መስተንግዶውም ሆነ ለተወዳዳሪዎቹ ድጋፍ ለመስጠት በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው የሚመቱ ታዳሚዎችም ለግጥሚያው ውበት ይሰጡታል።
በመጨረሻም አሸናፊው በዳኛው ተነግሮ ተፎካካሪዎችም ተቃቅፈው አዲሱን አመት በፍቅር ይጀምሩታል።