ብድር ላለመክፈል ሞቷን ፌስቡክ ላይ ያወጀችው ኢንዶኒዢያዊት እየተፈለገች ነው
ሊዛ ደዊ ፕራሚታ 2 ሚሊየን የኢንዶኔዥያ ሩፒ ወይም 270 ዶላር እዳዋ ለማምለጥ ነው በሞት ያሟረተችው
ፌስቡክ ላይ በመኪና አደጋ ህይወቷ እንዳለፈ የሚያሳዩ ምስሎችን በልጇ በኩል ያስለጠፈችው ፕራሚታ ከእዳዋ ያመለጠች ቢመስላትም ፖሊስ በተደራራቢ ወንጀል እየፈለጋት ነው
ብድር ላለመክፈል ሞቷን ፌስቡክ ላይ ያወጀችው ኢንዶኒዢያዊት እየተፈለገች ነው።
ቃል በገቡት እለት የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ ያልቻሉ ሰዎች የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው ጊዜ ለመግዛት ሲሞክሩ ይታያል።
የተለያዩ የሀሰት ሰበቦችን የሚደረድሩና ስልክ በመዝጋት አድራሻቸውን የሚያጠፉም ጥቂት አይደሉም።
ከወደ ኢንዶኒዥያ የተሰማው ዜና ግን ከተለመደው ረቀቅ ያለና አጃኢብ ያሰኘም ነው።
የ270 ዶላር ብድር ላለመክፈል ፌስቡክ ላይ “መሞቷን” የሚያሳዩ ምስሎችን አቀነባብራ በልጇ የፌስቡክ ገጽ እንዲለጠፍ ያደረገችው ሊዛ ዴዊ ፕራሚታ መነጋገሪያ ሆናለች።
ማያ ጉናዋ ከተባለች ግለሰብ 2 ሚሊየን የኢንዶኒዥያ ሩፒ ወይም 270 ዶላር የተበደረችው ሊዛ፥ ብድሩን ለፈለገችው አላማ ካዋለች በኋላ መመለሱ ከብዷታል። እናም ለአበዳሪዋ ጊዜ ስጪኝ የሚል ተማጽኖ ታቀርባለች።
የሁለት ሳምንት ጊዜ የተሰጣት ፕራሚታ በህዳር 20 2022 መክፈል የነበረባትን እዳ በታህሳስ 6 2022ም መክፈል አልቻለችም።
ይባስ ብላም ከአበዳሪዋ የሚደወልላትን የስልክ ጥሪ ማንሳትና መልዕክት መመለስ አቆመች።
ታህሳስ 11 2022 ላይም ፌስቡክ ላይ አስደንጋጭ ምስልን በልጇ በኩል ለቀቀች፤ በአሳዛኝ የትራፊክ አደጋ ህይወቷ ማለፉን የሚገልጽ መልዕክትም ከምስሉ ጋር ተያይዟል።
ምስሉ ሊዛ ደዊ ፕራሚታ አፍንጫዋ ላይ ጥጥ ተደርጎ እንደሞተ ሰው ተገንዛ የሚያሳይ በመሆኑ አበዳሪዋን ጨምሮ ብዙዎች አዝነዋል።
የፕራሚታ የቀብር ስነስርአት ይካሄድበታል የተባለው ቦታ ከመኖሪያ መንደሯ እጅግ መራቅ ግን አበዳሪዋን ጥርጣሬ ውስጥ ከተተ።
እናም ጉንዋን የፌስቡክ ምስሎቹን ትክክለኛነት ወደማጣራት ገባች፤ በዚህም ፕሪሚታ ከጎግል ያወረደችውን ምስል ተጠቅማ ሞቻለሁ መለቷንና ሁሉም ነገር እዳዋን ለማምለጥ የተደረገ ማጭበርበር መሆኑን ደረሰችበት።
የፕራሚታ ልጅም እናቱ በሞት ያሟረተችው ከእዳ ነጻ ለመሆን ፈልጋ ነው፤ ሁሉንም ነገር ያቀነባበረችው እሷ ናት ብሏል።
ከ270 ዶላር እዳ ለማምለጥ በፌስቡክ ሞቷን ያወጀችው ሊዛ ደዊ ፕራሚታ ከነጭራሹ ደብዛዋን አጥፍታ በፖሊስ እየተፈለገች ነው።
ከእዳዋ ያመለጠች የመሰላት ፕራሚታ በሌላ ወንጀል በፖሊስም እየታደነች ነው ተብሏል።