በልደታቸውን ቀን የመጀመሪያ ልጃቸውን ያገኙት አሜሪካውያን ጥንዶች
ሶስቱ የቤተሰብ አባላት ልደታቸውን በተመሳሳይ ቀን በማክበር ከ133 ሺ ሰዎች ለአንዱ የሚሳካውን እድል አግኝተዋል
በአላባማ የሚገኘው የሀንትስቲል ሆስፒታል አስገራሚውን ግጥምጥሞሽ ካጋራ በኋላ ጥንዶቹ በማህበራዊ ሚዲያ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት እየጎረፈላቸው ነው
አሜሪካውያን ጥንዶች ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ልጃቸውን አግኝተዋል።
የአላባማ ነዋሪዎቹ ካሲዲ እና ዲይላን ስኮት በልደታቸው ቀን ልጅ ማግኘታቸው ደስታቸውን ድርብ አድርጎታል።
ሌለን የሚል ስም የወጣላት ህጻን በቀጣዩ አመት ከወላጆቿ ጋር ልደቷን ታከብራለች።
ይህ ግጥምጥሞሽም ከ133 ሺህ ሰዎች ውስጥ ለአንዱ የሚሳካ ነው ይላሉ የሀንትስቲል ሆስፒታል ሀኪሞች።
ሆስፒታሉ አንድ የልደት ቀንን ስለተጋሩት እድለኛ ቤተሰቦች በፌስቡክ ገጹ ላይ መረጃና ምስል ካጋራ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ደስታቸውን ገልጸዋል።
አንድ ልጅ ከወላጆቹ የአንዱን የልደት ቀን የመጋራት እድሉ 1/365ኛ ወይም 0.0027 በመቶ ነው።
የኦሎምፒክ ሜዳሊያን የመሸለም እድልም 1 ለ662 ሺህ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የስፖርት ውድድሮች ድረ ገጹ ቡኪስ ዶት ኮም መረጃ እንደሚያሳየው ሚሊየን ዶላሮችን የሚያስገኝ የጃክፖት ሎተሪ የማሸንፍ እድል የሚኖረው ከ320 ሚሊየን ሰዎች አንዱ ነው።
ከ133 ሺህ ሰዎች ለአንዱ የሚሳካውን እድል ያገኙት የአላባማ ነዋሪዎቹ ጥንዶች በገና በዓል ሰሞን በልደታቸው ቀን ያገኟት ሴት ልጃቸው ከአለም አስተዋውቃቸዋለች።