ዳኞች አዲሱን ካርድ መጠቀም የሚጀምሩት አሜሪካ በሰኔ ወር በምታዘጋጀው የ2024 የኮፓ አሜሪካ ውድድር ነው
የደቡብ አሜሪካ እግርኳስ ማህበር ከቀይና ቢጫ ካርዶች ባሻገር ሮዝ ካርድ ጥቅም ላይ እንዲውል ወስኗል።
አሜሪካ ከሰኔ 20 2024 ጀምሮ በምታዘጋጀው የኮፓ አሜሪካ ውድድርም ዳኞቹ አዲሱን ካርድ ይዘው ወደሜዳ ይገባሉ ተብሏል።
የፍቅር መገለጫ የሆነው ቀለም የያዘው ካርድ በሜዳ ላይ ሲመዘዝም ፍቅርና መቆርቆርን አመላካች ሆኗል።
የደቡብ አሜሪካ እግርኳስ ማህበር ያሳለፈው ውሳኔ የተጫዋቾችን ደህንነት ለማስጠበቅ ትልድ ድርሻ እንደሚኖረው ዴይሊ ሜል አስነብቧል።
ሮዝ ካርድ የሚመዘዘው ለማንና ለምንድን ነው?
በኮፓ አሜሪካ አህጉራዊ ውድድር ጥቅም ላይ መዋል የሚጀምረው ሮዝ ካርድ በጨዋታ ሂደት የጭንቅላት ግጭትና ራስን መሳት በሚያጋጥመበት ጊዜ ነው።
ተጫዋቼ ከባድ ጉዳት ገጥሞታል ያለ አሰልጣኝ ለዋናው ወይም አራተኛው ዳኛ ተናግሮ ዳኛው ካመነበት በሮዝ ካርድ እንዲወጣ ማድረግ ይችላል።
የአለማቀፉ የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) በአንድ ጨዋታ ከአምስት በላይ ተጫዋቾችን መቀየር እንደማይቻል በህግ መደንገጉ ይታወቃል።
አዲሱ ሮዝ ካርድ ግን አምስት ተጫዋቾች ከተቀየሩ በኋላ ሊገጥም የሚችል ከባድ ጉዳትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
በአሰልጣኞች ጥያቄ ሮዝ ካርድ የሚመዘዝበት ተጫዋች ከሜዳ ሲወጣ ተቃራኒው ቡድንም ስድስተኛውን የተጫዋች ቅያሪ እንዲያደርግ ይፈቀድለታል። ይህም የጨዋታውን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ያግዛል ተብሏል።
በሮዝ ካርድ ከሜዳ የሚወጣው ጉዳት የደረሰበት ተጫዋች በቀጥታ ወደ መልበሻ ክፍል ያመራና የህክምና ክትትሉን ይጀምራል።
የቡድኑ ሀኪሞችም ለደቡብ አሜሪካ እግርኳስ ማህበር የህክምና ኮሚሽን በ24 ስአት ውስጥ የተጫዋቹን ጤንነት በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ይህም ጉዳት የደረሰባቸው ተጫዋቾች በአሰልጣኞች ግፊት በደንብ ሳያገግሙ እንዳይሰለፉ ያደርጋል ነው የተባለው።