የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ፊፋ 'ሰማያዊ ካርድ' የመጠቀም ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወም ተናግረዋል
የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ፊፋ አለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ቦርድ ያቀረበውን 'ሰማያዊ ካርድ' የመጠቀም ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወም ተናግረዋል።
ኢንፋንቲኖ ጉዳዩ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት መረጃው ነበረኝ ብለዋል።
የእግር ኳስ ህጎችን የሚያወጣው ቦርዱ፣ ዳኞች ያጠፉ ተጨዋቾችን ለ10 ደቂቃ ከጨዋታ ውጭ ሆነው እንዲቆዩ የሚያደርገውን የ'ሰማያዊ ካርድ' ሀሳብ በሶኮትላንድ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከፊፋ ጋር መክሮበታል ተብሏል።
በበርዱ ስብሰባ የተገኙት ኢንፋንቲኖ "በከፍተኛ እግርኳስ ደረጃ ሰማያዊ ካርድ መኖር የለበትም። በዚህ ጉዳይ ልንነጋገር አይገባም" ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
"ፊፋ ሙሉ በሙሉ የሰማያዊ ካርድ ጥቅም ላይ መዋልን ይቃወማል። እንደፊፋ ፕሬዝደንት በዚህ ጉዳይ ላይ የማውቀው የለም። ፊፋ በቦርዱ ውሳኔ ላይ የመሳተፍ መብት አለው።"
ፊፋ አዳዲስ ሀሳቦችን ለመቀበል ሁልጊዜም ክፍት ነው ያሉት ኢንፋንቲኖ ነገርግን የእግርኳስን የቆዩ አሰራሮችን እና ልምዶችን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።ኢንፋንቲኖ "ሰማያዊ ካርድ የሚባል የለም" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።