ከሰሞኑ በሱዳን ምስራቃዊ ክፍል በተነሳ ተቃውሞ ምክንያትሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ውስጥ ትገኛለች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሱዳን አሁን ባጋጠማት የውስጥ ችግሯ ላይ በግልጽ ወይም በድብቅ የሚደረግ የውጭ ጣልቃገብነትን መፍቀድ የለባትም ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ከሰሞኑ በሱዳን ምስራቃዊ ክፍል በተነሳ ተቃውሞ ምክንያትሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡
በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ክስተት በጎ በሆነ መልኩና በወንድማዊነት እየተከታተሉት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ኃይሎች “ውስጣዊ ግጨት ውስጥ ስንገባ ወይም የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያጋጥመን፤ የእነዚህን ኃይች የማጥቃት ፍላጎት ሲበዛ እናያለን” ብለዋል፡፡
- “የሱዳን ጦር ከጥቅምት 6 ጀምሮ ከገባበት መሬት ለቆ እንዲወጣ” ኢትዮጵያ ጠየቀች
- ምስራቅ ሱዳን ተገቢውን ፖለቲካዊ ውክልና እና ጥቅም የማያገኝ ከሆነ ራሱን የቻለ ሀገር ይሆናል- የቤጃ ጎሳ መሪ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ኃይሎች ሉአላዊነታችንን በመጣስ ፍላጎታቸውን ለመጫንና ለመጥቃት ጉጉት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ሱዳን ያጋጠማት ችግር በራሷ ጥበብ እንድትፈታው የተመኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሱዳን ያለ ውጭ ጣልቃ ገብት በራሷ ተቋማት “ለውስጣዊ ችግሯ ውስጣዊ መፍትሄ እንደምታገኝ ተስፋ አለን” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ እያጋጠመው ያለመረጋጋት ሁኔታ፤ በተለይም ኢትዮጵያና ሱዳን ለዜጎቻቸው ዲሞክራሲ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እየፈተነው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ከባለፈው አመት ጥቅምት ጀምሮ በመካሰስ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፤ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል “ለህግማስከበር ዘመቻ”ሲሄድ የነበረውን ክፍተት በመጠቀም፤ሱዳን የኢትዮጵያ ሉአላዊ ድምበር በመጣስ ወረራ ፈጽማለች ሲል ይከሳል፤ የሱዳን መንግስት ይህን ክስ አይቀበልም፡፡
በለፈው ሳምንት ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባለፈው ህዳር ወር የደህንነት ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ጎረቤት ሱዳን የአለምአቀፍ ሕግን በመጣስ ኢትዮጵያን መውረሯንና ወረራው እስካሁን መቀጠሉን ለተመድ ገለጸዋል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗንም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የሱዳን አካሄዱን በፍጥነት እስካልቀየርን ድረስ፣ ይህም ሌላው አፍሪካን የማተራመስ እና የአፍሪካውያንን ዕጣ ፈንታ ወደ ከፋ የመብት ጥሰት የሚያሸጋግር ምዕራፍ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ገለጸዋል፡፡