ምስራቅ ሱዳን ተገቢውን ፖለቲካዊ ውክልና እና ጥቅም የማያገኝ ከሆነ ራሱን የቻለ ሀገር ይሆናል- የቤጃ ጎሳ መሪ
በምስራቃዊ ሱዳን ከሰሞኑ አመጽ መቀስቀሱ የሚታወስ ነው
ጎሳ መሪው ለጥያቄዎቻቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል
ፍትሃዊ ውክልና እና ተጠቃሚነት የማይኖር ከሆነ የሱዳን አካል ሆነው መቀጠል እንደማይፈልጉ በምስራቅ ሱዳን የሚገኙ የቤጃ ጎሳ አባላት አስታወቁ፡፡
አባላቱ አለን ከሚሉት የፍትሐዊነት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ የሱዳን መንግስትን በመቃወም ወደ አደባባዮች ወጥተዋል፡፡
ፖርት ሱዳን (ወደቡን)፣ አየር ማረፊያውን መዝጋትን ጨምሮ በምስራቃዊ ሱዳን የሚደረጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ማገዳቸውም ነው የተነገረው፡፡
ወደ ፖርት ሱዳንና ሱዋኪን ወደቦች የሚወስደው መንገድ በሬድሲ ግዛት አቃባን ጨምሮ በሶስት ቦታዎች ላይ የተዘጋ ሲሆን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘው ኦሲፍ መንገድም በተቃውሞ መዘጋቱ ተገልጿል፡፡
ከሬድ ሲግዛት በተጨማሪ በከሰላ ግዛት በሁለት ቦታዎችና በገዳሪፍ ግዛት በሶስት ቦታዎች መዘጋቱም ተዘግቧል፡፡
ምስራቃዊ ሱዳን የገዳሪፍ፣ የከሰላ እና የፖርት ሱዳን ግዛቶችን ያካትታል፡፡
በአካባቢው በኤርትራ ጭምር የሚኖሩ የቤጃ ጎሳ አባላትን ጨምሮ የሃደንደዋ እና ሌሎችም ጎሳዎች ይኖሩበታል፡፡
በዋናነት በአካባቢው የሚነሱት ጥያቄዎች ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በምስራቅ ሱዳን ያሉ ሶስት ግዛቶች በአንድ ተጠቃለው የራሳቸውን እጣ ፋንታ ራሳቸው ይወስኑ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምስራቅ ሱዳን ተገቢውን ሃገራዊ ውክልና ያኝኝ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ይኑር የሚል ነው፡፡
- የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ሙከራን ተከትሎ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች እየተካሰሱ ነው
- “የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
ምስራቅ ሱዳን፤ ሱዳን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት “ከ1956 ጀምሮ በልማት የተገለለ እና ወደኋላ የቀረ አካባቢ ነው” ሲሉ ትናንት ከአል አረቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት የቤጃ ጎሳ አባላት መሪ መሃመድ አል አሚን ትሪክ ለረጅም አመታት ስናቀርባቸው የነበሩ ጥያቄዎቻችን በአስቸኳይ እንዲመለሱ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ምስራቅ ሱዳን የሱዳን አካል ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ ጥያቄዎቹ ተመልሰው ተገቢውን ውክልና እና ጥቅም ሊያገኝ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን እንወስናለን፤ ራሳችንን የምናስተዳድርም ይሆናል ነው ትሪክ ያሉት፡፡
“ይህ በሆነበት ሁኔታ ምስራቅ ሱዳን ራሱን የቻለ ሀገር ይሆናል፤ ወይም አሁን ያለው ፍትሃዊ ያልሆነ አሰራር ተስተካክሎ ከሱዳን ጋር እንቀጥላለን” ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡ ለዚህ የሚሆን አቅም እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
በሱዳን ከሰሞኑ ባለስልጣናቱ አክሽፈነዋል ያሉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡