”በድንበር አካባቢ ድልድዮች እየገነባ” ያለው የሱዳን ጦር ድርጊቱን እንዲያቆም ተነግሮታል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ለቆ እንዲወጣ በድጋሚ አሳስበዋል
የሱዳን ጦር፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ድልድዮች እየገነባ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሱዳን ጦር ድንበር አካባቢ ድልድዮች እየገነባ ቢሆንም ድርጊቱ እንደማያዋጣ ለካርቱም እንደተነገራት አስታውቀዋል፡፡
“ድርጊቱ አያዋጣም እረፉ ብለናቸዋልን” ያሉት ቃል አቀባዩ ከድልድዮች ባለፈም ሲሱዳ ወታደራዊ ሰፈሮችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር ከጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ከገባበት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ማሰሰቧ የሚታወስ ሲሆን እስካሁን ግን ይህ አለመሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ባላት የድንበር ችግር ድርድርና ንግግርን እንደምታስቀድም ገልጸው ይህ የሚሆነው ግን የሱዳን ጦር ወደ ከጥቅምት 2013 በፊት ወደነበረው ቦታው ተመልሶ አካባቢው ሰላማዊ ሲሆን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ድልድዮችንና ወታደራዊ ሰፈሮችን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንደማይጠቅምና ከዚህ ድርጊትም መቆጠብ እንደሚገባት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የድንበሩን ጉዳይ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስረዳች መሆኑን የገለፁት አምባሳደር ዲና፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ገለፃ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የፖለቲካ እና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ትናንት በተወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሱዳን ጦር አርሶ አደሮችን የማሳደድ፤ ንብረትን የማቃጠልና የመዝረፍ ተግባራት ሲፈጽም እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡