የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ሙከራን ተከትሎ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች እየተካሰሱ ነው
የሲቪል አስተዳድሩ “ወታደራዊ አመራሩ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር እያደናቀፈ ነው” ብለዋል
ወታደራዊ አመራሩ “የሲቪል አስተዳድር ፖለቲከኞች ለመፈንቅለ መንግስቱ መሞከር በር ከፍተዋል” ሲል ከሷል
የነፃነት እና የለውጥ ሀይል ጥምረት በመባል የሚጠራው የሱዳን የሲቪል አስተዳድር ፖለቲከኞች ወታደራዊ አመራሩ ያወጣዉን መግለጫ ማውገዛቸው ተሰምቷል።
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሰጡት መግለጫ “የሰቪል አስተዳድር ፖለቲከኞች ለመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ምክንያት ናቸው” ማለታቸው ይታወቃል።
ምከትል አዛዡ አህመት ዳጋሉ በበኩላቸው “ፖለቲከኞች የሱዳን ጦር አምባገነኑን የአልበሽር ስርዓት በመገርሰስ የከፈለውን መስዋዕት ረስተው ጦሩን ማናናቃቸው መፈንቅለ መንግስት እንዲፈጸም በር ከፍተዋል” ሲሉ የሲቪል አስተዳድሩን ተችተዋል።
- የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ዙሪያ የሲቪል አስተዳድር ፖለቲከኞችን ወቀሱ
- “የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
የነፃነት እና የለውጥ ሀይል ጥምረት በመባል የሚጠራው የሲቪል አስተዳደር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና ምከትል አዛዡ አህመት ዳጋሉ ንግግርን አውግዟል።
የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ከሸፈውን መፍንቅለ መንግስት አስመልክተው ያደረጉት ንግግር ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር የሚጎዳ እና የሱዳንን አብዮት የሚቃረን ነው ብሏል።
“የሱዳን የሽግግር ጊዜ መሰረቶች እንዲናጉ አንፈቅድም” ያለው ጥምረቱ፤ “ለዚህም በሙሉ ሀይላችን እንታገላለን” ብሏል በመግለጫው።
በሱዳን መከላከያ ሰራዊት እና የፀጥታ ሀይሉ ላይ የሚደረጉ የሪፎርም ስራዎች እንዲፋጠኑ የጠየቀው ጥምረቱ፤ “ርዝራዦች” ሲል የጠራቸው ሀይሎችን የማፅዳት ስራው ሊፋጠን ይገባልም ብሏል።
ጥምረቱ በመግለጫው አክሎም በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ላይ የሚደረገው የምርመራ ውጤት በአፋጣኝ ለህዝቡ ይፋ ሊደረግ ይገባል ያለ ሲሆን፤ በተግባሩ የተሳተፉ የሲቪል አመራሮች ዝርዝርም ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል።
በተያያዘ ዜና የቤጃ ጎሳ አባላት የሆኑ ተቃዋሚዎች ባነሱት ተቃውሞ የፖርት ሱዳን የአውሮፕላን ማረፊያን መዝጋታቸው ተስመቷል።
ተቃዋሚዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ በምስራቅ ሱዳን ያሉ ወደቦችን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገኘውን መንገድ መዝጋታቸውም የሚታወስ ሲሆን፤ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው የቤጃ ጎሳ አባላት የሚኖሩበት ግዛት ኋላ ቀር ነው የሚል መሆኑ ተነግሯል።