ጠ/ሚ ዐቢይ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ አካላት ባስተላለፉት መልእክት ምን አሉ?
ጠ/ሚ ዐቢይ በባህርዳር በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ድልድይ መርቀዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ ባደረጉት ንግግርም “መገዳደል፣ ጥፋትና የማያሽገር ጉዞ ይብቃን” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ አካላት ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር በመሆን ከአራት አመት ተኩል በፊት ግንባታው የተጀመረውን የአባይ ድልድይን ዛሬ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት ባድረጉት ንግግር “የባርዳር ከተማ ነዋሪዎች እና የብልጽግና አመራሮች ፊት ሆኜ በጫካ ለሚገኙ ወንድሞቻችን ጥሪ ማስተላለፍ እወዳለሁ” ብለዋል።
“አማራ አረጋ ከበደን የመሰለ ታማኝና ትጉህ መሪ አአግኝቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አማራን የሚልና ለአማራ መብት እንቆረቆራለሁ በማለት ጫካ የገባችሁ ወንድሞች ከአረጋ መስተዳድር ስር ሆኖ ህዝቡን እና ክልሉን መጥቀም ይችላል” ብለዋል።
“መገዳደልና መጠፋፋት ይብቃን” ያሉ ሲሆን፤ “አላስፈላጊ እና ኢትዮጵያን የማያሻር ጉዞ፣ የኢትጵያን ህዝቦች በእኩል የማያከብር ጉዞ ስለማይጠቅመን ኑ ወደ ክልለችሁ ተመለሱ፣ ከልላችሁን አልሙ ሰላማችሁን ጠብቁ፤ ያንን ስታደርጉ እኛም ከልብ ከጎናችሁ ሆነን አብረናችሁ እንሰራለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “በማይገባ ነገር መገዳደል ይብቀን” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የ"ፋኖ" ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ገደማ ጊዜ ቀርቶታል።
የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ንጹሀን ዜጎች ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ተመድን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል።
የፌደራል መንግሥት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።