በ8 ወራት ከ80 በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት አስታወቀ
በባሕር ዳር እሁድ በተፈጸመ ጥቃት 4 የአንድ ቤተሰብ አባልትን ጨምሮ 5 ሙስሊሞች መገደላቸው አስታውቋል
ምክር ቤቱ “በመንግስትና ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት የእስልምና እምነት ተከታዮችን አደጋ ላይ ጥሏል” ብሏል
በአማራ ከልል ባለፉት 8 ወራት በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ80 በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውንም የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫው፤ ባለፉት ስምንት ወራት በአማራ ክልል መንግትና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ተከትሎ የእስልምና እምነት ተከታዮችን አደጋ ላይ መጣሉን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው አክሎም፤ በኃይል ንጹሃን ዜጎችን ማገትና መሰወር እንዲሁም መግደል ከቀን ወደ ቀን እየተበራከተ በመምጣት የክልሉን ህዝብ በተለይም ሙስሊሙን ማህበረሰብ መከራ ውስጥ ጨምሮታል ብሏል።
ለአብነትም ባሳለፍነው እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በባህዳር ከተማ ቀበሌ 14 የመቅሪብ ሰላት ሰግደው ወደ ቤታቸው በሚመለሱ አማኞች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አራት የአንድ ቤሰተብ አባላትና አንድ ጎረቤታቸውን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
በተመሳሳይ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሞጣ ከተማ አንድን ወጣት ካገቱ በኋላ ቤተሰቦቹን በማስፈራራት 300 ሺህ ብር ከተቀበሉ በኋላ ታጋቹን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው መጣላቸውንም ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው።
መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ማክሰኚት አካባቢ 4 የእስልምና እምነት ተከታዮች መገደላቸውንም ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
በቢቸና ከተማም መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ንጹሃን ባልና ሚስት ለምን ለመንግስት ግብር ከፈላችሁ በሚል በግፍ እንደተገደሉም የምክር ቤቱ መግለጫ አመላክቷል።
በአጠቃላይ በክልሉ ባለፉት 8 ወራት ከ80 በለይ ሙስሊሞች ተገድለዋል ያለው ምክር ቤቱ፤ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች መፈናቀላቸውንም አስታውቋል።
እንዲሁም 47 ሰዎች መታገታቸውን እና ከ260 በላይ ዝርፊያዎች መፈጻማቸውንም ነው ምክር ቤቱ በመግለጫው ያመላከተው።
በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ፣ ስቃይ፣ እንግልት መገደል እና መፈናቀልንም በጽኑ እንደሚያወግዝም የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫው አስታውቋል።
“ይህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ግፍ እና ግድያ ለዘመናት አብሮ እና ኅብረት ፈጥሮ የኖረዉን የሕዝባችንን አብሮነት ለማናጋት የታሰበ ስለሆነ በጋራ እንታገለው” ሲልም ጥሪ አስተላልፏል።
እነዚህንም ጥቃቶች ለማስቆም መንግሥት፣ የክልሉ ሕዝብ የሌላ እምነት ተከታዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የበኩላቸውንም እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፏል።