የአፍሪካ የመድሃኒት ኤጀንሲ ማቋቋሚያን ያልፈረሙ አገራት እንዲፈርሙ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ
ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ አገራት ይሄንን የማቋቋሚያ ሰነድ እስካሁን አልፈረሙም
የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የህብረቱ የመድሃኒት ኤጀንሲ እንዲቋቋም ተስማምተው ነበር
የአፍሪካ የመድሃኒት ኤጀንሲ ማቋቋሚያን ያልፈረሙ አገራት እንዲፈርሙ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ፡፡
የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ባካሄዱት 32ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ የመድሃኒት ኤጀንሲ እንዲቋቋም ወስነው ነበር፡፡
ይህ ተቋም ከአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል በመቀጠል ሁለተኛው የጤና ተቋም ሲሆን ወደ አህጉሪቱ የሚገቡ መድሃኒቶችን ደህንነት መቆጣጠር፣ በአፍሪካ የሚመረቱ መድሃኒቶችን ጥራት ማሳደግ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ የዚህ ተቋም ዋነኛ ስራ ይሆናል ተብሏል፡፡
ይሁንና ተቋሙን ለመመስረት የግድ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ስምምነቱን መፈረም እና የአገራቸው አንድ ህግ እንዲሆን ማጽደቅ ያስፈልግ ነበር፡፡
ስምምነቱን የፈረሙ አገራት 28 ሲሆኑ 25 አገራት ደግሞ ስምምነቱን እስካሁን አለመፈረማቸውን በአፍሪካ ህብረት የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር ሳሜቴ ሲዙማ ሚናታ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑን የአፍሪካ አገራት ይሄንን ጠቃሚ ተቋም እንዲመሰረት ስምምነቱን እንዲፈርሙ ኮሚሽነሯ ከ35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ ላይ አሳስበዋል፡፡
ከምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል እስካሁን ስምምነቱን የፈረሙት ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ብቻ ሲሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአጠቃላይ 25 አገራት ስምምነቱን አልፈረሙም ተብሏል፡፡
የሰሜን አፍሪካ አገራት በአንጻራዊነት በተሻለ ደረጃ ስምምነቱን ፈርመዋል ተብሏል፡፡
ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ጋና፣ ቱኒዝያ፣ ዚምባብዌ እና ናሚቢያ ይሄንን ስምምነት ከፈረሙ እና የአገራቸው ህግ እንዲሆን ካጸደቁ አገራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጀሪያ ደግሞ ስምምነቱን ያልፈረሙ እና የአገራቸው ህግ እንዲሆን ካላጸደቁ አገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸውም ተብሏል፡፡