አፍሪካ በጸጥታው ም/ቤት እንድትወከል የጠየቁት ጠ/ሚ ዐቢይ በዛሬው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ንግግር ያደርጋሉ
ማኪ ሳል በህብረቱ ሊቀመንበርነት በሚሰየሙበት በዚህ ጉባዔ የእስራኤል የታዛቢነት ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝም ይጠበቃል
ጠ/ሚ ዐቢይ በጉባዔው የመክፈቻ ንግግራቸው የአፍሪካን የጸጥታው ምክር ቤት የውክልና ጥያቄ በድጋሚ እንደሚያነሱ ይጠበቃል
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 28 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ይጀመራል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ጉባዔ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በአካል ተገኝተው የሚያካሂዱት ይሆናል፡፡
ጉባዔው “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል ዛሬና ነገ የሚካሄድ ነው።
በጉባዔው ለመሳተፍም የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
መሪዎቹ በህብረቱ ተልዕኮዎች እና በአጀንዳ 2063 አፈጻጸም ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎውን ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲን ተክተው ሊቀመንበርነቱን እንደሚረከቡም የሚጠበቅ ነው፡፡
እስራኤል በህብረቱ የታዛቢነት ሚና እንዲኖራት በቀረበው ጥያቄም ላይ የውሳኔ ሃሳብ ይሰጣል፡፡
የህብረቱ የዓመቱ (እ.ኤ.አ 2022) መሪ ቃል ቀርቦ የሚጸድቀውም በዚሁ ጉባዔ ነው፡፡
በጉባዔው መክፈቻ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዲሁም ተሰናባቹንና አዲሱን የህብረቱን ሊቀመናብርት ጨምሮ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ እንዲሁም የአረብ ሊግ አባል ሃገራት ዋና ጸሃፊ ግብጻዊው አቡል ጌይት ንግግር እንደሚያደርጉ አል ዐይን አማርኛ ከህብረቱ ያገኘው የጉባዔው መርሃ ግብር ያሳያል፡፡
መላው ጥቁር ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ከአሁን ቀደም ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ድምጽ እና መቀመጫ እንዲኖራት የሚቀርበውን ጥሪ መቀበላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ጥያቄ በዛሬው ንግግራቸው እንደሚያነሱትና ጉባዔውም እንደሚወያይበት ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የልዩ ልዩ ተቋማት ኃላፊዎች የተሳተፉበት 40ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ከጉባዔው ቀደም ብሎ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
የዛሬው የመሪዎቹ ጉባዔ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ባቀረባቸው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቦች ላይ እንደሚመክርም ይጠበቃል ተብሏል፡፡