”ዛሬ ጎረቤታችንን የጎበኘ እሳት ነገ ቤታችንን ማንኳኳቱ አይቀርም።”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ”አጥፊዎችን ፊትለፊት”መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል
የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተ ረብሻ ለሞቱት ንጹሃን ሀዘናቸውን ገልጸዋል
የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተ ረብሻ ለሞቱት ንጹሃን ሀዘናቸውን ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “አጥፊዎቹን ፊት ለፊት እስካልተጋፈጥናቸው ድረስ የሚያደርሱትን ችግር በመሸሽ ብቻ አናመልጠውም” ማለታቸውን ኢቢሲ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አንገትን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ በመቅበር መፍትሔ የምናገኝበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ላለማየት ጭንቅላትን ጎሬ ውስጥ በመቅበር ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ዛሬ ጎረቤታችንን የጎበኘ እሳት ነገ ቤታችንን ማንኳኳቱ አይቀርም።”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተፈጠረ ረብሻ ህይወታቸውን ላጡ ንጹሀን ዜጎች ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ጥቃት አድራሽ ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
የእርስበእርስ የመጠላለፍና የመገዳደል ባህል ሊቆም ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ሕዝብ እንዲበጣበጥ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሣ፣ አንዱ ሌላውን እንዲገድል” ለዘመናት የተዘራውንና እየፈነዳ ያለውን የልዩነት መርዝ መለየትና ማክሸፍ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
እንደጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጻ “ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ በየሚዲያው ‹በለው፣ በለው› የሚሉ አካላትን አሁን በግልጽ”ተለይተዋል፡፡
በረብሻው በአዲስአባባና በኦሮሚያ ክልል 239 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡