በታዋቂው አርቲስት ግድያ ምክንያት የተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት በከፊል ተለቀቀ
በታዋቂው አርቲስት ግድያ ምክንያት የተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት በከፊል ተለቀቀ
ከሁለት ሳምንታት በፊት ከታዋቂው የኦሮምኛ ቋንቋ ሙዚቀኛ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ተዘግቶ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ከትናንት ከሰአት በኃላ ጀምሮ በከፊል ተለቋል፡፡
“የብሮድባንድና የዋይፋይ” አገልግት ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መስራት ጀምሯል፡፡ አገልግቱ በመላው ሀገሪቱ የተቋረጠ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ ስለመለቀቁ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ነገርግን በተለያዩ ክልሎች ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም ጀምረዋል፤ ይህ በክልሎችም “የብሮድባንድና የዋይፋይ” አገልግሎት መጀመሩን ያመለክታል፡፡
የሞባይል ዳታ እስካሁን ያልተለቀቀ ሲሆን መቼ እንደሚለቀቅም ማወቅ አልተቻለም፡፡
መንግስት የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እንዳይስፋፋ በማሰብ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ማቋረጡ ምክንያታዊ መሆኑን ሲገልጽ ኢንተርኔት ተጠቅመው ይሰሩ የነበሩ ተቋማትም ስራ አቁመው ቆይተዋል፡፡
አርቲስቱ በአዲስ አበባ ገላን አካባቢ መገደሉን ተከትሎ በተነሳ ብጥብጥ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ160 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡
ከሰው ህይወት መጥፋት ባሻገር በክልሉ በተለይም በምእራብ አርሲ በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማትም ውድመት እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ባቀረበረው ሪፖርት መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአርቲስቱ ግድያ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፖሊስ ምርመራ እያካሄደባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡