ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለመሙላት ያቀደችው 4.9 ቢ/ሜ.ኪ ውሃ ከግድቡ የግንባታ ሂደት ጋር እየተከናወነ ነው
በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል የሚደረገው ድርድር እንደሚቀጥልም ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል
የውሃ ሙሌቱ የግድቡን ተፈጥሯዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለመሙላት ያቀደችው 4.9 ቢ/ሜ.ኪ ውሃ ከግድቡ የግንባታ ሂደት ጋር እየተከናወነ ነው
የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ትናንት ለሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት በተመለከተ የገለጹት ሀሳብ በተሳሳተ መልኩ መተርጎሙን አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን “ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት ጀመረች” ብለው የሰሩትን ዘገባ ነው በተሳሳተ መልኩ ተተርጉሞብኛል ያሉት፡፡
የግድቡ የዉሃ ሙሌት ከግንባታው ሂደት ጋር ጎን ለጎን የሚከናወን መሆኑን ነው ሚኒስትሩ በትናንትናው መግለጫቸው ያብራሩት፡፡
ሙሌቱን በተመለከተ የሚኒስትሩ መግለጫ
አምና የግንባታው ከፍታ 525 ሜትር በነበረበት ወቅት ክረምት ላይ ዉሀ በላዩ ላይ ያልፍ እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ አሁን ላይ ከፍታው 560 ሜትር በመድረሱ ለዘንድሮ የሚያስፈልገውን ዉሃ ለመያዝ ያስችላል ብለዋል፡፡ በግድቡ የዉሃ ሙሌት ሂደት ዉሃው እስከተገነባው 560 ሜ. ሞልቶ በላዩ ላይ ወደመፍሰስ ያመራልም ነው ያሉት፡፡ “እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የዉሃው መጠን አይወርድም” ያሉት ሚኒስትሩ ፣ “የተገነባው የግድቡ ኮንክሪት ካልተነሳ በስተቀር ዉሀው በላዩ ላይ ነው የሚያልፈው” ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚፈልግ ሲሆን “ይሄን መሙላት ግዴታ ነው ፤ ማንም ሊለውጠው አይችልም” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
ከመግለጫቸው በኋላ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የግድቡ የግንባታ ከፍታ 560 ሜ. መድረሱን ገልጸው አሁን ካለው ከፍተኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ ወደ ግድቡ የሚገባው ዉሃ ከሚወጣው በመብለጡ በተፈጥሯዊ መንገድ ሙሌቱ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህም ዉሃው በቅርቡ ሞልቶ በግድቡ አናት ላይ እስኪያልፍ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የግንባታ ሂደቱም እስከ 640 ሜ. ከፍታ ጎን ለጎን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የግድቡን የዉሃ ሙሌት በተመለከተ በሳተላይት የሚታዩ ምስሎች ትክክለኛ መሆናቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲው ሴንቲኔል-1 ከቀናት በፊት የግድቡ የዉሃ ሙሌት መጀመሩን የተመለከተ የሳተላይት ምስል አውጥቷል፡፡ ይሄን ምስል መነሻ ያደረጉ ትንታኔዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሰጡም ነበር፡፡
የሴንቲኔል-1 የሳተላይት ምስል-ፎቶ ከአሶሼትድ ፕሬስ
የውሃ ሙሌቱ ተፈጥሯዊ ሂደትን በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
አሁን በሳተላይት የታየው የዉሃ ሙሌት ከክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ እንጂ በመንግስት ዉሳኔ ከዉሃው ማስተላለፊያ ቦዮች የተወሰኑት ተዘግተው የተከናወነ ስለ አለመሆኑ የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ ከአውሮፓውያኑ 2012 ወዲህ ሲከታተሉ የቆዩት ዶ/ር ኬቪን ህዊለር ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን የደረሰውን የግንባታ ከፍታ መነሻ በማድረግ ዶ/ር ኬቪን እንደሚሉት “ዉሀውን ግድቡ እስከ ደረሰበት የከፍታ ልክ ከመሙላት የሚያግድ አንዳችም ነገር የለም”፡፡
ምንም እንኳን ቦዮች ባይዘጉም ከክረምቱ ጋር ተያይዞ አልፎ ከሚሄደው ዉሃ በግድቡ ተይዞ የሚቀረው እንደሚበልጥ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በትዊተራቸው ያሰፈሩት ጽሁፍ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ዶ/ር ኬቪን ገለጻ በግድቡ የሚቋጠረውን የዉሀ መጠን ለመጨመር መንግስት የተወሰኑ ቦዮችን መዝጋት ይችላል፡፡ ሆኖም ክረምቱ በራሱ የግድቡን ተፈጥራዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ ሙሌቱ እንዲከናወን እያደረገ በመሆኑ አሁን ላይ ቦይ መዝጋት ብዙም አስፈላጊ ሊሆን እንደማይችል ዶ/ር ኬቪን ይገልጻሉ፡፡
የግንባታው ሂደት የደረሰበት ደረጃ በመጀመሪያው የዉሃ ሙሌት ለማከናወን የታቀደውን የ4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመያዝያዝ የሚያስችል መሆኑን የዉሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ ይሄም የመጀመሪያ 2 ተርባይኖችን የኃይል ማመንጨት ስራ ለመሞከር የሚያስችል ነው፡፡ “ሙሌቱ ከግድቡ ዲዛይን እና ከዕቅዳችን ጋር ተያይዞ ይቀጥላል” ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ከሙሌቱ ጋር በተያያዘ ማንም ፈቃጅ እና ከልካይ የለም ብለዋል፡፡
ግንባታው የደረሰበት ደረጃ በራሱ ግድቡ በተፈጥሮ ሂደት ብቻም ቢሆን መሞላቱ እንደማይቀር የሚያደርገው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ዉሀ ለመያዝ ቦይ መዝጋት የሚያስፈልገው የሙሌቱን ሂደት ለማፋጠን ፣ አሊያም የወንዙ የዉሃ መጠን በሚያንስበት ወቅት ነው፡፡
የድርድሩ ቀጣይነት
የድርድሩ ትኩረትም በዉሃ ሙሌት ላይ ያተኮረ ሳይሆን በድርቅ ወቅት ዉሃ እንዴት እንደሚለቀቅ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ዶ/ር ኢ/ር አብራርተዋል፡፡ መግባባት ላይ ለመድረስ ግን የሶስትዮሽ ድርድሩ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በድርድሩም ሂደት መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ባልተግባቡባቸው ነጥቦች ዙርያ የየሀገራቱ ሪፖርቶች ለአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ፕሬዘዳንት ቀርበዋል ብለዋል፡፡ ሪፖርቶቹን ተመልክተው የተደራዳሪዎቹ ሀገራት መሪዎች በሚያስተላልፏቸው መመሪያዎች መሰረት ድርድሩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የምታደርገው ድርድር የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውንም ትውልድ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልከ የሚደረግ እንደሆነም አብራርተዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ 1,800 ሜትር ርዝመት እና ከ145 እስከ 170 ሜትር የመጨረሻ ከፍታ የሚኖረው ሲሆን አጠቃላይ የሚይዘው የዉሃ መጠንም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡