የህዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ተጠናቋል - ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ4ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የቴክኒክ ባለሙያዎች ድርድር በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል
የህዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ4ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ኢትዮጵያውያን ተባብረን በመሥራታችን ፈጣሪ ረድቶናል፤ በገንዘባችሁ፣ በዕውቀታችሁ፣ በጉልበታችሁና በጸሎታችሁ በሥራው ውስጥ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በግድቡ ግንባታ ያሳዩትን ህብረት በሌሎች ጉዳዮችም እንዲደግሙትም ጠይቀዋል።
በግድቡ ግንባታ ከውስጥን ከውጭም ጫናዎች እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናዎችን በመቋቋም ለዚህ ስኬት ደርሰናል ብለዋል።
“ለግድቡ የምናደርገውን ማናቸውንም ድጋፍ እስከ ፍጻሜው እንድንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰኔ ወር 2015 ከህዝብ እንደራሴዎች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ “ኢትዮጵያ የሱዳን እና ግብፅን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የህዳሴ ግድብ ሙሌቱ እስከ መስከረም መጀመሪያ አታከናውንም" ማለታቸው ይታወሳል።
ከአንድ ወር በፊት በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በካይሮ በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ሲመክሩም ይሄው የህዳሴው ግድብ ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ነበር።
በዚህ ምክክር መሪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዳግም ለመጀመር መስማማታቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።
የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ድርድር በቅርቡ በግብጽ መዲና ካይሮ ዳግም ሲጀመርም ሀገራቱ በቀጣይ ስለሚያደርጓቸው ድርድሮች፣ የመወያያ አጀንዳዎች እና በሶስቱ ሀገራት ልዩነቶች ዙሪያ መምከራቸው አይዘነጋም።
የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ቀጣይ ውይይታቸውን በአዲስ አበባ መስከረም ወር ውስጥ ለማካሄድ ቀጠሮ መያዛቸውም ተገልጿል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።