መንግስት በፍራንኳ ቫሉታ ምክንያት 33 ቢሊዮን ብር ማጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
የግብርና ስራዎችን ለማሻሻል በሚል መንግስት ለግል ባለሀብቱ 73 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንም ገልጿል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነው
መንግስት በፍራንኳ ቫሉታ ምክንያት 33 ቢሊዮን ብር ማጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህን ያሉት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ፣በየአካባቢው ባሉ ግጭቶች እና አሁን ደግሞ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተፈተነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢኮኖሚቀውን ለማነቃቃትም መንግስታቸው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርት እጥረት እንዳይገጥም ማድረግ ዋነኛ ስራ መሆኑን አክለዋል፡፡
ለአብነትም መንግስት ፍራንኳ ቫሉታ የተባለውን ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬ ከየትኛውም ቦታ በማምጣት ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ መፍቀድ ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡
በዚህ አሰራር መሰረትም ምንግስት ከዚህ አሰራር ማግኘት የነበረበትን 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የግብርና ምርትን ለመጨመርም መንግስት 200 ቢሊዮን ብር ለግሉ ባለሃብት ብድር የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 73 ቢሊዮን ብር በግብርና ስራ ለተሰማሩ አልሚዎች መሰጠቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የወጪ ንግድን በሚመለከትም ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከቡና ንግድ 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከአትክልት እና ፍራፍሬ ወጪ ንግድ ደግሞ 82 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት 33 በመቶ ላይ ደርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ተጨማሪ የወጋ ማረጋጋት ስራዎችን እንደሚሰራም አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ ከተጀመሩት ስራዎች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም የስኳር ፋብሪካዎችን በሚመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ቁጥሩን ወደ 135 ከፍ ማድረግ መቻሉን እና ዓመታዊ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅሙን ከዚህ በፊት ከነበረው 6 ሚሊዮን አሁን ላይ 20 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡
የሜጋ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ሳይስተጓጎሉ እንደቀጠሉ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮይሻ ሀይል ማመንጫ ግንባታ 46 በመቶ ሲደርስ የህዳሴ ግድቡ ግንባታም በተቀመጠለት የጊዜ መርሃ ግብር በመከናወን ላይ ነውም ብለዋል፡፡
የስኳር ፋብሪካዎችን ቁጥር እና የማምረት አቅምን ለማሳደግ በተያዘው እቅድ መሰረትም አሁን ላይ የስኳር ፋብሪካዎች ቁጥር 9 ሲደርስ ዓመታዊ የማምረት አቅማቸውንም ወደ 360 ሺህ ቶን ማሳደግ መቻሉንም አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቂቃዎች በኋላ በጸጥታ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡