የዩክሬን ጦርነት “ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት” ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ባንክ አስጠነቀቀ
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት “በብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ ውድቀት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው” ብለዋል
በፈረንጆቹ 2021 እና በ2024 መካከል የዓለም ቁጠባ በ2 ነጥብ 7 በመቶ ይንሳል ተብሏል
የዩክሬን ጦርነት ቀድሞውንም የተናወጠውና በኮቪድ ወረርሺኝ የተመታው የዓለም ኢኮኖሚ፤ ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ባንክ አስጠነቀቀ፡፡
“የኢኮኖሚ ውድቀቱ” በተለይም በደምብ ባላደጉ የአውሮፓና ምስራቅ እስያ ሀገራት የከፋ እንደሆነም ተቋሙ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዘገባው የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ መልፓስ፡ ‘ስታግፍሌሽን’ ተብሎ የሚታወቀው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መኖርና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ዴቪድ መልፓስ “የዩክሬን ጦርነት፣ በቻይና ያለው ተጽእኖ (ኮቪድ-19)፣ የአቅርቦት መቆራረጥ፣ በጥሬ እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት የዓለም ኢኮኖሚ እያዳከሙት ነው፣ በዚህም በብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ ውድቀት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው ”ም ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ደካማ የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴ ምክንያት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የሚኖረው የኢኮኖሚ አድገት ዝቅተኛ ሆኖ ይቀጥላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም አሁን ያለው ከፍተኛ የዋጋ ንረትና የአቅረቦት እጥረት ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑ አንስተዋል፡፡
የዓለም ባንክ ለዩክሬን የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ የሚሆን 1 ነጥብ 5 ዶላር ድጋፍ አጽድቋል፡፡ ድጋፉ ተቋሙ ለዩክሬን ሊሰጠው ያሰበውን የ 4 ቢሊዮን ዶላር አካል ነው ተብሏል፡፡
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በ2022 ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ካጋጠማቸው ሀገራት ዩክሬን እና ሩሲያ ይጠቀሳሉ፡፡
እንደ ደቪድ መልፓስ በፈረንጆቹ 2021 እና በ2024 መካከል የዓለም ቁጠባ በ2 ነጥብ 7 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን ፤ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆሉ በፈረንጆቹ 1976 እና በ1979 መካከል ከታየው የኢኮኖሚ ውድቀት በእጥፍ ያደገ ነው፡፡