ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፡ “ህይወታችሁን ለኛም፣ ለየትኛውም ፓርቲ አትስጡ”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የአዲስ አበባ ወጣቶች በምርጫ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣት የለባቸውም፤ ይልቁንም በድምጻቸው የሚፈልጉትን የሚመርጡበትና የማይፈልጉትን የሚቀጡበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርብ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበው የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበር
ናቸው፡፡
“የአዲስ አበባ ወጣቶች ብልጽግናን ከወደዳችሁት ድምጻችሁን ስጡት፤ ከጠላችሁት በድምጽ ቅጡት፤ ህይወታችሁን ለኛም፣ ለየትኛው ፓርቲ አትስጡ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሚለኒየም አዳራሽ ለተሰበሰቡት ወጣቶች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ወጣቶች ምርጫን ተካትሎ በሚመጣ ጦስ ሰለባ ሲሆኑ እንጂ ፖለቲከኞች የችግሩ ሰላባ ሲሆኑ አይታይም፤ በመሆኑም ወጣቶችን አጋድለው ስልጣን ለመያዝ በሚፈልጉ አካላት መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡
“የብልጽግናን ሀሳብ በሚቀጥሉት 50 እና 60 አመታት በፍፁም ማሸነፍ አይቻልም፤ አትሳሳቱ፡፡ ዓብይን ግን ማሸነፍ ይቻላል፡፡ “
ማንም ስልጣን ቢይዝ ለብልጽግና ጠንክሮ ካልሰራ ከ6 ወር በላይ ሀገር መምራት አይችልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር( ኢህአዴግ) በግንባርነት ሀገሪቱን ለ27 አመታት ከመራ በኋላ ከ4ቱ የግንባሩ አባላት ሶስቱ ማለትም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦረሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ( ደኢህዴን) በመዋሀድ የብልጽግና ፓርቲን መስርተዋል፡፡
ከግንባሩ አባለት መካከል ህወሓት ከውህደቱ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል፡፡
ፓርቲዎቹ ለመዋሀዳቸው እንደዋነኛ ምክንያት የሚያነሱት “አጋር ፓርቲዎች” እና የሚወክሉትን ህዝብ አግላይ መሆኑ በመታመኑና ተደጋጋሚ ጥያቄ በመነሳቱ ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ 50 ሚሊዮን ህዝብ ይሳተፍበታል ብሎ ለሚጠብቀው ምርጫ 2012 ዝግጅት እያደረደ መሆኑን ገልጿል፡፡