ጠ/ሚ ዐቢይ ኮሽ ሲል ጣልቃ መግባት ይፈልጋሉ ያሏቸውን የውጭ ኃይሎች አስጠነቀቁ
የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን በማበጣበጥ የሚያገኙት ትርፍ አይኖርም ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ያሏቸውን ኃይሎች በስም አልጠቀሱም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ውሰጥ "ኮሽ ባለ ቁጥር" በውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ይፈልጋሉ ያሏቸውን የውጭ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቁ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሃላላ ኬላ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት መድረክ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
- የሰላም ንግግር ሂደቱ “ብዙ ጣልቃገብነት” እንዳጋጠመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
- ጠ/ሚ ዐቢይ “በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው” ያሉ አካላትን አስጠነቀቁ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው "መፈትፈት የሚፈልጉ ኃይሎች በተለይም ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስባለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።
የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን በማበጣበጥ የሚያገኙት ትርፍ አይኖርም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ እነዚህ የውጭ ኃይሎች "የኛን ጉዳይ ለኛ ትተው፣ በርከት ያለ ያልሰሩት ጉዳይ ስላላቸው ራሳቸው በምድራቸው መስራት" አለባቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ያሏቸውን ኃይሎች በስም አልጠቀሱም።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት በሰላም ስምምነት ከቆመ ወራትን አስቆጥሯል።
በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ለሁለት አመት የቆየው ግጭት በኘሪቶሪያ በተፈረመው የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊቆም ችሏል።
በትግራይም በፌደራል መንግስቱ እውቅና ያለው ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ተመስርቷል።
መንግስት ከህወሓት ጋር በሽብርተኝነት ፈርጆት ከነበረው ሸኔ ወይም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እያለ ከሚጠራው ቡድን ጋርም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በታንዛኒያ ድርድር መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።
አሁን ላይ ድርድሩ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከየትኛውም ወገን መግለጫ አልሰጠም።
መንግስት የትግራይን ጉዳይ በስምምነት የቋጨና ከሸኔ ጋር እየተደራደረ ቢሆንም በአማራ ክልል መንግስት ካሳለፈው ልዩ ኃይልን የማፍረስና "መልሶ የማደራጀት" ውሳኔ ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሯል።
ልዩ ኃይል መፍረስ የለበትም የሚሉ የተቃውሞ ሰልፎች በአብዛኛው የክልሉ ትላልቅ ከተሞች መካሄዳቸው ይታወሳል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፖርቲ ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ተገድለዋል።
መንግስት ለግድያው ጽንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርጓል፤ በእነዚህ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገልጿል።
ነገርግን የኢትዮጵያ ለዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፖርቲ(ኢዜማ) እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) ግድያውን አውግዘው ግድያው በፍትህ አካላት እንዲጣራ እና መንግስት በግድው ዙሪያ ፍረጃ እንዲያቆም መጠየቃቸው ይታወሳል።
መንግስት ከትናንት በስትያ ባወጣው መግለጫ በክልሉ እና በፌደራል መንግስቱ ላይ ችግር እንዲፈጠር አድርገዋል ያላቸውና በውጭ የሚኖሩ ግለሰቦች ተላልፈው እንዲሰጡት መጠየቁን ገልጿል።