ጠ/ሚ ዐቢይ “በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው” ያሉ አካላትን አስጠነቀቁ
"ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች በማለት ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ነው" ብለዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ “የወንድማማች ሀገራትን ግንኙነት የሚያሻክር የሃሰት ውንጀላም ኢትዮጵያ በጽኑ ታወግዛለች” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ አስጠነቀቁ።
በሱዳን ጦር እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ 6ኛ ቀኑን ይዟል።
ጦርነቱን ተከትሎም የተለያዩ ሀገራት በጦርነቱ የተለያዩ ድጋፍን እየሰጡ ነው፤ የኢትዮጵያ ሰራዊትም የሱዳንን ድንበር አልፎ ገብቷል የሚሉ መረጃዎች ተሰራጭተው ነበር።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በአረብኛ ቋንቋ ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት "ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች በማለት ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም "ኢትዮጵያ አሁን ሱዳን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለድንበር ውዝግቡ መጠቀሚያ ልታደርገው አትፈልግም" ሲሉም አስታውቀዋል።
ወንድም የሆነው የሱዳን ሕዝብ እንዲህ ላሉት ሐሰተኛ ወሬዎች ጆሮ እንደማይሰጥ እምነታችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሀገራትን ግንኙነት የሚያሻክር የሃሰት ውንጀላም ኢትዮጵያ በጽኑ እንደምታወግዘው አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም “አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት "ሉዓላዊነቷን በመጣስና መሬቷን በኃይል በመቆጣጠር የፈጸሙትን ድርጊት ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ አትፈጽመም" ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ያለው ጉዳይም በውይይት እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑንም በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሱዳን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በአረብኛ ባወጡት መግለጫ፤ ተፋላሚ ወገኖች ውጊያቸውን በማቆም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበው እንደነበረ ይታወሳል።