ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ግብጽን እየጎበኙ ነው
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግብጽ በአፍሪካ ተደማጭ አገር መሆኗን ተናግረዋል
ማኪ ሳል ከሳምንት በኋላ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ከዲ.አር ኮንጎ ይረከባሉ
የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ግብዣ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ግብጽ ይገኛሉ፡፡
ማኪ ሳል ካይሮ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ሲሲ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፤ በሁለትዮሽ እና ሌሎች ጉዳዮችም ላይ ተወያይተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን አል ሲሲ ሃገራቸው በማኪ ሳል የአፍሪካ ህብረት አመራርነት ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸውና ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እና አሳሪ ከሆነ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ ለቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መግለጻቸውንም ሲሲ ተናግረዋል፡፡
የናይል ውሃ ለተፋሰሱ አገራት የትብብር አጀንዳ እና ህይወት መሆኑን ለሴኔጋሉ አቻቸው መናገራቸውንም አል ዐይን ከካይሮ ዘግቧል፡፡
ማኪ ሳል በተያዘው የ2022 የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ቦታን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ፊሊፕ ሼሽኬዲ ከቀናት በኋላ እንደሚረከቡ ይጠበቃል፡፡
በመግለጫው ባደረጉት ንግግርም ግብጽ በአፍሪካ ተደማጭ አገር ናት ብለዋል፡፡ ከሲሲ ጋር በነበራቸው ውይይት ስለ አህጉራዊ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች፣ ስለ ኮሮና ቫይረስ የክትባቶች ሁኔታ እና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማንሳታቸውን የገለጹም ሲሆን ግብጽ የኮሮና ክትባቶችን ለማምረት የቻለች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሃገር መሆኗን አድንቀዋል፡፡
ማኪ ሳል ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሢመት ላይ ከተገኙ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች መካከል መሆናቸው ይታወሳል፡፡