የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ “ሱዳናውያንን ግራ አጋብቷል” ተባለ
የሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ “በሱዳን የፖለቲካ መሪዎች መካከል የነበረው ፍጥጫ የከፋ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ሁነኛ ማሳያ ነው” ተብሏል
የሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ ሱዳንን “ወደ ለየለት ቀውስ ይወስዳታል” የሚል የበርካቶች ስጋት ሆነዋል
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ከስልጣን መልቀቃቸው በትናትናው እለት በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “ከስልጣናቸው የለቀቁት ከሀገሪቱ ጦር ጋር የተካሄደውን የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ስምምነት በማብቃቱ”መሆኑ በምክንያትነት አቅርቧል፡፡
"ሀገራችን ወደ አደጋ እንዳትገባ የምችለውን ያህል ሞከርኩ፤ አሁን ግን ከጠቅላይ ሚኒስትርነቴ በመልቀቅ ለሌላ የዚህች ክቡር ሀገር ወንድ ወይም ሴት እድል ለመስጠት ወሰንኩ"ም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብደላ ሃምዶክ፡፡
የሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ ከአዲስ መንግስት ምስረታ ጋር በተያያዘ በሲቪል እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል ለሳምንታት የዘለቀው ፍጥጫ የከፋ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ሁነኛ ማሳያ መሆኑ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላሂ ሃምዶክ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ መጠየቃቸውን ተከትሎ በሱዳን ግራ መጋባት መስፈኑ እየተገለጸ ነው።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ የስራ መልቀቅ ጥያቄ በሱዳን ፀጥታ እና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ፍራቻ ያደረባቸው በርካታ ሱዳናውያን አሉ፡፡
በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ካላቸው ተቀባይነት እና ተወዳጅነት እንጻር ከስልጣን ቢለቁ የሁኔታውን እውነታ በምንም መልኩ አይለውጥም የሚሉ ድምጾች በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡
ከሁለቱም እሳቤዎች በተለየ መልኩ በዚህ ሰፊ ልዩነት ውስጥ ሀገሪቱን ከሁከትና ብጥብጥ ለመታደግ የሚቀጥለውን ደረጃ በጥበብ ማስተናገድ እና መባባሱን ማቆም እንደሚያስፈልግ የሚገነዘቡ እንዳሉም ሲገለጽ ይስተዋላል፡፡
ከአል-ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉት ሱዳናዊቷ መምህርት ሳሚያ ሰዲክ፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅ በሀገራቸው ቀጣይ እጣ ፈንታ ከፍተኛ ስጋት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ተናግሯል፡፡
ሳሚያ ሰዲክ "ሃምዶክ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላ በጣም ያሳስበናል፣ ሀገራችን አደጋ ላይ ትገኛለች፣ በተለይ በቡዱኖች መካከል ያለው የአቋም ልዩነት ወደ ለየለት ግጭት እንዳይወስደን እንፈራለን” ብሏል፡፤
"የሃምዶክ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት መልቀቅ ማለት የፖለቲካው ግጭት ይቀጥላል ማለት ነው፤ ይህም ማለት የኑሮ ሁኔታ እንዲበላሽና ስቃያችንን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው" ሲሉም ያላቸውን ስጋት አክሏል መምህርት ሳሚያ ሰዲክ፡፡
በአንጻሩ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከስልጣን መልቀቅ በሱዳን የሚያሳድረው አንዳች ተጽእኖ የለም ያለው ደግሞ ወጣቱ ሱዳናዊ አህመድ ኢብራሂም ነው፡፡
አህመድ ኢብራሀም ለአል-ዐይን እንደገለጸው " የሃምዶክ መልቀቅ ብዙ አያሳስበንም ፤ አሁን ከመሃል መንገድ አንመለስም እናም ግባችን እስክናሳካ ድረስ የጀመርነውን ሰላማዊ ተቃውሞ አጠናክረን እንቀጥልበታለን" ሲል ተናግሯል፡፡
የሱዳኑ የናሽናል ኡማ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አል ዋቲክ አል-ባረር በበኩላቸው፡ የሃምዶክ የስራ መልቀቂያ በሚቀጥሉት ሰአታት ውስጥ ትልቅ ፖለቲካዊ እና ህገ-መንግስታዊ ዉጤት የሚያመጣ እንደሚሆን ያለውን እምነት አስቀምጧል።
“የሃምዶክ እርምጃ ሱዳንን በጊዜያዊነት ወደ ወታደራዊ አስተዳደር ይመልሳል ይሆናል፤ ነገር ግን ህዝባዊ ጫና እየቀጠለ በሄደ ቁጥር በስልጣን ላይ ያለው አመራር በአጭር ጊዜ የሲቪል ጠቅላይ ሚኒሰትር ሹመትን እንዲያፋጥን የሚያደርግ ይሆናል” ሲሉም ነው አል-ባረር ለአል-ዐይን የተናገሩት፡፡
አል-ባረር፡ የተቃውሞ ንቅናቄውን ሲመሩ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የአብዮታዊ የተቃውሞዎች ኮሚቴዎችም በሚቀጥሉት ሰዓታት ውስጥ በሚፈጠረው ሁኔታ ላይ የጋራ አቋም የሚይዙ ይሆናልም ብሏል።
በተመሳሳይ የሱዳን ኮንግረስ ፓርቲ ኦፊሴላዊ ቃል አቀባይ ኑረዲን ባቢከር፤ አሁን በሱዳን ላለው የፖለቲካ ቀውስ የጦር አዛዡን ዋና ተጠያቂ አድርጓል፡
ባቢከር"ሃምዶክ ከሉዓላዊው ምክር ቤት ሊቀመንበር ጋር ከተስማሙ በኋላ ወደ ቦታው ቢመለሱም በቦታው ላይ ምንም ለውጥ አላመጡም፤ ሰልፎቹ እና ተቃዉሞዎች ቀጥለው ነበር ፤ አሁን ከስልጣን መልቀቅ በኋላም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር መከሰቱ የማይቀር ነው" ሲሉ ተናግሯል፡፡
የሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ የአብዮቱን ይበልጥ ለማቀጣጠል የሚረዳ ነውም ብሏል፡፡
"በእኔ ግምት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቅ በኋላ ያለው የሲቪል ግንባር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆኗል" ሲሉም አክሏል ቃል አቀባዩ ኑረዲን ባቢከር።