ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሁለት ወር ሳይሞላቸው ስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ስልጣን እንደሚለቁ አስታወቁ።
ባለፈው ሀምሌ ከካቢኔያቸው እና ከፓርቲያቸው በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ከስልጣን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ተከትው ወደ ስልጣን የመጡት ሊዝ ትረስ ስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል፡፡
አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ መስከረም ወር ላይ በቅርቡ ህይወታቸው ባለፈው የብሪታንያ ንግስት ኤልሳቤት ነበር ሹመቱ የተሰጣቸው፡፡
ስልጣን ከያዙ ሁለት ወር ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ትረስ ስልጣን ለመልቀቅ መገደዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስልጣን ለመልቀቅ ያበቃቸው በመሪነት ጊዜያቸው ለመስራት የሚያስችላቸው ሁኔታ ውስጥ አይደለሁም በሚል ሲሆን አሁን ባለሁበት ሁኔታ ብቀጥል ቃል የገባሁትን መፈጸም አልችልም ማለታቸው ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ትረስ በብሪታንያ ያጋጠመውን የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለመፍታት በሚል የግብር ቅናሽ እንደሚያደርጉ ቢናገሩም ከፓርቲያቸው እና ከካቢኔ አባላቶቻቸው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
ይሄንን ተከትሎም የግምጃ ቤት ሚኒስትር እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮቻቸውን ከስራ ያገዱ ሲሆን ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ለህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት በመናገር ላይ ነበሩ፡፡
ይሁንና ምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎችን ለማድረግ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ከሰሞኑ የጠየቀ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አሳውቀዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ትረስ ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት አዲስ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾም ዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት በህዝበ ውሳኔ ከወጣችበት ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ በተፈጠሩ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ስራቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡