ዩክሬን ከ230 በላይ የኢራን ሰራሽ ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች
ሩሲያ ድሮኖቹን በመጠቀም የዩክሬን መሰረተ ልማቶች እያወደመች እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል
ዩክሬን ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ እያሰበችበት እንደሆነም ተገልጿል
ዩክሬን ከ230 በላይ የኢራን ሰራሽ ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስምንት ወራት የሞላው ሲሆን የጦርነቱ ሁኔታ በየጊዜው እየተቀያየረ አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ቀጥሏል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ እንዳሉት ኢራን ሰራሽ የሆኑ ከ233 በላይ ለሩሲያ የተሰጡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ተመተው መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ እነዚህን ኢራን ሰራሽድሮኖቹን በመጠቀም የዩክሬን መሰረተ ልማቶች እያወደመችበት እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በዛሬው ዕለት ብቻ 10 ድሮኖችን መትተው መጣላቸውን አክለዋል፡፡
ሩሲያ በተለይም የዩክሬን ዋና ዋና መሰረተ ልማቶችን እያወደመች እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በተለይም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው የዩክሬን የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች ከሀይል አቅርቦት ውጪ ሆነዋል የተባለ ሲሆን ከተሞቹን መልሶ የሀይል አቅርቦት እንዲያገኙ ከፍተኛ ወጪ እየጠየቁ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡
ክሪሚያን ከተቀረው የሩሲያ ክፍል ጋር ለማስተሳሰር የሚውለው ድልድይ በዩክሬን ተመቶብኛል ያለችው ሞስኮ በ10 ቀናት ውስጥ ከ190 በላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በዩክሬን ላይ አድርሳለች ተብሏል፡፡
ሩሲያ በአጠቃላይ በ16 የዩክሬን ግዛቶች ላይ የሚሳኤል፣ የድሮን እና ሌሎች ጥቃቶችን ሰንዝራለች የተባለ ሲሆን ኢራን ሰራሽ ድሮኖች ዋነኛ የጥቃቱ መፈጸሚያ እንደሆኑ ዩክሬን አስታውቃለች፡፡
ዩክሬን ከመሰረተ ልማት ውድመት በተጨማሪ 70 ንጹሃን ዜጎቿ እንደተገደሉባት ያስታወቀች ሲሆን ኢራን ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርጋለች ስትልም ክስ አቅርባለች፡፡
ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን እንዳልሰጠች ብትገልጽም በትናንትናው ዕለት ሚሳኤል ለመስጠት ከሩሲያ ጋር ስምምነት መፈጸሟን ዓለም አቀፍ ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡