ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
ሰልፋ የተቀሰቀሰው የፌደራል መንግስት በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው
የፌደራል መንግስት መግለጫ የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ ፌደራል ወይም ወደ ክልል የጸጥታ መዋቅር እንዲካተቱ መወሰኑን እና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጿል
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሰልፋ የተቀሰቀሰው የፌደራል መንግስት በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ መዋቅሮች እንዲካተቱ ወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት በትናንትና መግለጫው አስታውቆ ነበር።
ነዋሪዎቹ የልዩ ሀይሉ አደረጃጀት ፈርሶ ወደ ፌደራል ወይም ክልል የጸጥታ መዋቅር ይካተት የሚለውን የመንግስት ውሳኔ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
አልዐይን አማርኛ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች አሁን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስሉ የወልደያ፣ ጎብዬ፣ ሰቆጣ እና ጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የወልደያ ከተማ ነዋሪ እንደተናገረው ከሆነ ከትናንት ጀምሮ በወልደያ እና አጎራባች ከተሞች ውጥረት መንገሱን ተናግሯል፡፡
ነዋሪው እንዳለው ትናንት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎብዬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለው የአማራ ልዩ ሀይልን ትጥቅ እንዲፈቱ መጠየቁን ተከትሎ አለመግባባት መከሰቱን ነግሮናል፡፡
በዚህ ካምፕ ውስጥ የነበረው ልዩ ሀይል ትጥቅ አንፈታም በሚል ከካምፕ በመውጣት ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከልዩ ሀይሉ ጎን ነን በሚል ወደ አደባባይ መውጣታቸውንም ይሄው ነዋሪ አክሏል፡፡
ከዛሬ ረፋድ ጀምሮም ወደ ወልደያም ሆነ ከወልደያ ወደ አጎራባች ወረዳዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መቆሙን የነገረን ነዋሪው በወልደያ ከተማ ባንኮችን ጨምሮ የግል እና የመንግስት ተቋማት መዘጋታቸውን ተናግሯል፡፡
ህዝቡ ስለ ህወሃት ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለው የሚለው ይህ ነዋሪ ህወሃት ለአራታኛ ዙር ጥቃት ሊከፍት የሚችል ከፍተኛ ስጋት ስላለበት የልዩ ሀይሉን ትጥቅ መፍታት ይቃወማል ብሏል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው እና ለደህንነቱ በመፍራት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ እንዳለን ከሆነ በሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ የነበረው የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቅ እንዲፈታ ከተነገው ጊዜ ጀምሮ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ልዩ ሀይል ከካምፕ በመውጣት ወደ ከተማዋ መግባቱን ነግሮናል፡፡
ልዩ ሀይሉ ከካምፕ መውጣቱን ተከትሎም የከተማው ነዋሪ ምግብ እና ውሃ እያዋጣ እየሰጠ መሆኑን የነገረን ይህ ነዋሪ ህዝቡ ከልዩ ሀይሉ ጎን መሆኑን በተለያየ መንገድ እያሳየ ነው ብሏል፡፡
ልዩ ሀይሉ ትጥቅ ፍታ መባሉ የአካባቢው ነዋሪ ከህወሃት ጥቃት ሊሰነዘርብን ይችላል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል የሚለው ይህ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ መንግስት ስለ ጉዳዩ ግልጽ እና አሳታፊ ውይይቶችን ከህዝቡ እና ከልዩ ሀይሉ ጋር ቢያደርግ የተሻለ ይሆናል ሲልም አክሏል፡፡
ዋግህምራ ዞን ስራ ባለችው ጻግብጂ ወረዳ የሚንቀሳቀሱ የአገው ሸንጎ ታጣቂዎች የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቅ ፍታ መባሉን ተከትሎ ወደ ሰቆጣ እና አካባቢው እሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ስልክ እየደወሉ እያስፈራሩ መሆኑን መስማቱንም ይሄው ነዋሪ ጠቅሷል፡፡
ሌላኛው የጎንደር ከተማ ነዋሪ በበኩሉ ትናንት ምሽት ከከተማው ራቅ ካሉ ወረዳዎች የነበሩ የልዩ ሀይል አባላት ወደ ከተማዋ ገብተዋል መባሉን እንደሰማ ነግሮናል፡፡
እነዚህ የልዩ ሀይል አባላትም ትጥቅ ፍቱ መባላቸውን በመቃወም ከካምፕ መውጣታቸውን እና ጥይት እየተኮሱ መምጣታቸውን ከመስማቱ በስተቀር በጎንደር ከተማ የተለየ እንቅስቃሴ እንደሌለም አክሏል፡፡
የፌደራል መንግስት ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የክልል ልዩ ሀይሎችን ወደ ፌደራል ወይም ወደ ክልል የጸጥታ መዋቅር እንዲካተቱ መወሰኑን እና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጿል።
መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ በሁሉም ክልል ልዩ ኃይሎች ላይ መሆኑን እና በአማራ ክልል ብቻ የተጀመረ ነው በሚል የተሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም ብሏል መንግስት።
የመንግስት ውሳኔ ከተቃዋሚ ፖርቲዎችም የተለያየ ተቃውሞ እያስናገደ ነው።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት በአማራ ልዩ ኃይሉ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበልና ልዩ ኃይሉም እንዳይበተን አሳስቧል።
መንግስት ልዩ ሀይሉን "የጋራ መግባባት እና መተማመን" ሳይደረስ ለማፍረስ መወሰኑ ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲል በጽኑ ተቃውሟል አብን።
በፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በክልሉ ልዩ ኃይል መካከል ውጥረት መንገሱን የገለጸው አብን መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ ጠይቋል።
"ቀጥተኛ እና ተገማች ጥቃት ያለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች" በመኖራቸው ውሳኔውን እንደማይቀበለው የገለጸው አብን ውሳኔ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ አለመረጋጋት የሚፈጥር ነው ብሏል።
ኢዜማ ህወሓት "በአማራ ክልል ስር ያሉ አካባቢዎችን" አስመልሳለሁ እያለ ባለበት ወቅት የመንግስት "በጥድፊያ እና በድብቅ" ወደ ተግባር መግባት ወቅታዊ አይደለም፤ውጤቱም አደገኛ ነው ብሏል።
ህወሓት ትጥቅ መፍታቱ ግልጽ ሳይሆን እና ድጋሚ የወረራ ስጋት ያለባቸው የትግራይ አዋሳኝ ክልሎች ባሉበት ሁኔታ መንግስት ቅደም ተከተል ማየት አለበት ብሏል።
ከሁለት አመት በፊት በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ካደረሰ በኋላ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በደረሱት ስምምነት መቆሙ ይታወሳል።
በትግራይ እና በአማራ ክልል ያሉ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ድጋሚ የግጭት መንሰኤ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለ።
የፌደራል መንግስት ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው "ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት" ለመገንባት ነው ሲል የውሳኔውን ተገቢነት ገልጿል።