ፖሊስ አራት ባሎችን ድል ባለ ሰርግ ያገባችውን ሴት አሰረ
እንስቷ ባሎቹ 100 ሺህ ዶላር ኪሳራ እንዲደርስባቸው አድርጋለች ተብሏል
እንስቷ ባሌ ለኔ ጊዜ ስለሌለው ተጨማሪ ባል ላገባ ችያለሁ ስትል ተናግራለች
ፖሊስ አራት ባሎችን ድል ባለ ሰርግ ያገባችውን ሴት አሰረ፡፡
የ35 ዓመቷ ቻይናዊት ባለትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ እናትም ነበረች። ይህች እንስት ከሰሞኑ በሀገሪቱ ፖሊስ ተይዛ መታሰሯን ተከትሎ በመላው ቻይና መነጋገሪያ ሆናለች።
ይህች ሴት በፖሊስ እንድትያዝ እና ለእስር የዳረጋት ነገር ተጨማሪ ሶስት ሰዎችን ድል ባለ ሰርግ አግብታለች በሚል ነው።
ትዳር እያላት ተጨማሪ ሶስት ሰዎችን ድል ባለ ሰርግ በአደባባይ ያከበረችው ይህች እንስት ድርጊቱን ለምን አደረግሽ ተብላ ስትጠየቅ ባሌ ሁሌ በስራ ምክንያት አብሮኝ የለም ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
ባለቤቴ በቢዝነስ ስራ ምክንያት ሁሌ አብሮኝ አይኖርም ይህን ያደረኩት ብቸኝነቴን ለማስወገድ ነውም ብላለች።
ጥሩ ገቢ እያላቸው እና መልካም የትዳር ህይወት እያላት ለምን ተጨማሪ ሶስት ባሎችን አገባች በሚል በመላው ቻይና ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል።
ይህች ስሟ ያልተጠቀሰችው እንስት ተክለሰውነቷ ውብ መሆኑ ወንዶቹ ብዙ ሳያጠኑ እና በፍጥነት እንዲያገቧት እንዳደረጋቸውም ተገልጿል።
እንስቷ አራቱንም ባሎቿን ፕሮግራም በማውጣት ታገኛቸው ነበር የተባለ ሲሆን ቀድሞ የነበራት ጋብቻ እንዳይታወቅባትን ሌሎች ጋብቻዎቿን ከማዘጋጃ ቤት ውጪ ባሉ ስርዓት እንዲፈጸም አድርጋለችም ተብሏል።
በሰርጎቿ እለትም ቤተሰብ እና ጓደኛ መስለው የሚተውኑ ሰዎችን አዘጋጅታለች የተባለችው ይህች እንስት በመጫረሻም ለእስር ተዳርጋለች ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
እንስቷ ለአንዱ ባሏ መንትያዎችን እንዳረገዘች እና መውለድ የምትፈልገው ወደ እናቷ ቤት በመሄድ መሆኑን መናገሯን ተከትሎ ጥርጣሬ ይፈጠራል።
የህክምና እና ሌሎች ወጪዎችን እንዲሸፍን የተጠየቀው አንዱ ባል መጠራጠር ይጀምራል።
ይህች እንስት ሌላኛው ባሏ ጋር ሆና ሀሰተኛ የህክምና ክትትል ማስረጃዎችን እና የተወለዱ ህጻናትን ፎቶዎች ስትልክ ነበርም ተብሏል።
ይህ ግለሰብም በመጨረሻ ባደረገው ማጣራት ሚስቴ ነች ያላት እንስት የሌሎች ሰዎችም መሆኗን ሲያውቅ ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰደው ተገልጿል።
አራቱም ባሎች በድምሩ የ100 ሺህ ዶላር ኪሳራ ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን ብዙ ለማትረፍ የጀመረቻቸው ማታለሎች በመጨረሻም ለእስር ዳርጓታል።