80 አመት በትዳር የቆዩት ጥንዶች የደስተኛ ትዳራቸውን ሚስጢር ይናገራሉ
የፒንሲልቫንያ ነዋሪዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ የጀመሩት ፍቅር ወደ ትዳር አድጎ ስምንት አስርት አመታትን ተሻግሯል
ጥንዶቹ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ስለተፈተነው የፍቅር እና የትዳር ህይወታቸው ወደኋላ መለስ ብለው ያወሳሉ
በ1936 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች እያሉ በፍቅር የተያዩት ጥንዶች ስምንት አስርት አመታትን በትዳር ቆይተዋል።
ከሰሞኑም 80ኛ አመት የትዳር በዓላቸውን በፒንሲልቫኒያ ላንካስተር አክብረዋል።
እድሜያቸው 102 አመት መድረሱ የተነገረላቸው ጥንዶች የ88 አመት የፍቅርና የትዳር ህይወታቸውን ያለምንም መዘንጋት ይተርካሉ።
ሮበርት የክፍል ጓደኛውን ኢዲዝ ስቻውም ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳዩዋት እንደወደዷት ይናገራሉ።
እናም ኳስ ይመለከቱ ዘንድ ይጋብዟታል፤ በወቅቱ ሳይነጋገሩ የተግባቡት ታዳጊዎች ግንኙነታቸው ፊልሞችን አብሮ ወደማየትና ደጋግሞ ወደመገናኘት ተሸጋገረ።
ሮበርት በፈረንጆቹ በ1942 ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ ለስቻውም የትዳር ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።
የህይወቴ ትክክለኛ አጋር ነው ብለው ያመኑበት ስቻውም አላቅማሙም፤ ተጋቡ።
በወጣትነታቸው የተመኙዋትን ያገኙት ሮበርት ትዳራቸውን ማጣጣም እንደጀመሩ ግን ሁለተኛው የአለም ጦርነት ወደ ፓስፊክ እንዲያቀኑ አስገደዳቸው።
አንድ አመት ያልደፈነው ትዳር በፍቅር እምባ በተሞሉ ደብዳቤዎች መገለጡ ግድ ሆነ።
የመጀመሪያ ልጃቸውን በ1944 ቢያገኙም ጦርነት ላይ የነበሩት አባት የማየት እድል አላገኙም።
“አንድም ቀን በጦርነቱ ይሞታል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ እንደሚመለስ እርግጠኛ ነበርኩ” የሚሉት ስቻውም ምኞታቸው በርግጥም ተሳክቶላቸው ሮበርት ከሞት አምልጥው ተመለሱ።
ቦምብ በሚዘንብበት ጦርነት ተተኳሽ መሳሪያ የሚያቀብሉት ሮበርት “ሁሌም ስለሚስቴ ነበር የማስበው” ይላሉ።
በ1949 ሁለተኛ ልጃቸውን ፓውላ ያገኑት ጥንዶች ከጦርነቱ ማግስት በላንካስተር ጎጆ ቀልሰው መኖር ጀምረዋል።
ቤታችን በፍቅርና ደስታ የተሞላ ነው የምትለው ፓውላ፥ በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ጓደኞቿ በፍቅር አብረው ማደጋቸውን ትገልጻለች።
ወላጆቼ አንድም ቀን ሲጨቃጨቁ አይታ እንደማታውቅም ነው ለላንካስተር ኦንላይን የተናገረችው።
ሮበርትም በፍቅርና በትዳር 86 አመታት የቆየንበት ምንም የተለየ ሚስጢር የለውም፤ አንዳችን ለአንዳችን ፈጥነን መድረሳችን ነው ይላሉ።
“ወደ መኝታ ክፍላችን ምንም አይነት መጥፎ ስሜት ይዘን አንገባም” የሚሉት ሮበርት፥ እንዳዩዋት የወደዷትን ባለቤታቸውን ለደቂቃዎችም ማስከፋት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ።
በ1981 ጡረታ ከወጡ በኋላ ወደተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ያደርጓቸው ጉብኝቶች እና የጎልፍ ጨዋታም የፍቅር ግንኙነታቸውን ለማደስ እንዳገዛቸው ነው የሚገልጹት።
ከሁለት አመት በፊት 100ኛ አመት ልደታቸውን ያከበሩት ጥንዶች አሁንም እርጅና የማይሸፍነው ፍቅራቸው ፊታቸው ላይ ይነበባል።
በ102 አመታቸው ሁለተኛ ፎቅ የሚወጡ የሚወርዱት፤ መኪና የሚነዱት ሮበርት እና ባለቤታቸው ረጅም የትዳር ህይወት ካላቸው ጥንዶች መካከል ስማቸውን አስፈረዋል።
በትዳር ህይወት 86 አመት ከ290 ቀናት የቆየው የሀርበርት እና ዘልመይራ ፊሸር የትዳር ህይወት በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ረጅሙ ትዳር ሆኖ መመዝገቡን ዩ ፒ አይ አስታውሷል።