የሽግግር መንግስቱ በፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ይመራል ተብሏል
በማሊ የፖለቲካ ኃይሎች በ 18 ወራት የሽግግር ጊዜ ላይ ተስማሙ
በማሊ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሽግግር ጊዜ ለ 18 ወራት የሚቆይ ሲሆን ሕዝቦች የማዳን ብሔራዊ ኮሚቴ (ሲኤንኤስፒ/CNSP) በሚል በተቋቋመው ኮሚቴ እንደሚመራ ተገልጿል፡፡ ኮሚቴው በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ መሆኑንም ሁሉን የፖለቲካ ኃይሎች የተሳተፉበት የብሔራዊ ምክክር መድረክ አጠቃላይ ሪፖርተር ሙሳ ካማራ ተናግረዋል፡፡
ከሶስት ቀናት ምክክር በኋላ ከተለያዩ የሀገሪቱ ኃይሎች የተውጣጡ 500 ያህል ተሳታፊዎች ባጸደቁት የሽግግር ቻርተር መሠረት የሽግግሩ ፕሬዝዳንት ወታደራዊም አሊያም ሲቪል ሊሆን ይችላል፡፡
ከሽግግሩ ፕሬዝዳንት እና ከምክትል ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ በአሁኑ ህገ-መንግስት መሠረት በሽግግሩ ፕሬዝዳንት በሚሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት ቢበዛ 25 አባላት ያሉት መንግስት ይቋቋማል፡፡
እንዲሁም በሽግግሩ ወቅት ከፖለቲካ ኃይሎች የተውጣጡ 121 አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት የሕግ አውጭ አካል ሆኖ ይቋቋማል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የ ሲኤንኤስፒ/CNSP ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ባደረጉት ከሶስት ቀናት ምክክር በኋላ የተደረሰውን ስምምነት በደስታ ተቀብለው የመፈንቅለ ምንግስቱ መሪዎች በተሳታፊዎች ለተዘጋጁ ሰነዶች ትግበራ አጥብቆ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡
በባማኮ አቅራቢያ በካቲ በሚገኘው በሳውንዲያታ ካቲ ካምፕ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 18 ቀን የተፈፀመውን የአመጽ ድርጊት ተከትሎ የማሊ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬይታ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ባውባው ሲሴ ከስልጣን ተወግደው በካምፑ ታስረው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ኬታ በዚያው ምሽት በፈቃዳቸው ሥራ መልቀቃቸውን ፣ እንዲሁም መንግሥታቸው እና የብሔራዊ ምክር ቤቱ መፍረሱን አስታውቀዋል፡፡
የማሊ ጎረቤቶች አገሪቱ ወደ ትርምስ ልትገባ ትችላለች በሚል ስጋት ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ የስጋታቸው ምንጭም ከስምንት ዓመታት በፊት በተፈጸመ የመሳሳይ ድርጊት የፈጠራቸው ጂሃዲስቶች እስካሁንም ኒጀር እና ቡርኪናፋሶን ቀውስ ዉስጥ እንዲቆዩ ማድረጉ ነው፡፡
የምዕራብ አፍሪካ 15 ሀገራትን ያቀፈው የኤኮኖሚ ማህበረሰብ-ኢኮዋስ የማሊ የጦር መኮንኖች በ 12 ወራቶች ውስጥ ስልጣን እንድያስረከቡ በአጽንኦት ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም የማሊ አጎራባች ሀገራት ድንበሮችን በመዝጋት 19 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ካላት ከሀገሪቱጋር የንግድ ልውውጥን አግዷል፡፡
የማሊ ጎረቤቶች የ18 ወራት የሽግግር መንግሥት ዕቅድን በተመለከተ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ገና ግልጽ አይደለም ፡፡
የማሊ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት ከኢኮዋስ የሀገራት መሪዎች ጋር በአክራ እንደሚገኙ አንድ የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን ለኤኤፍፒ ገልፀዋል፡፡