በማሊ የሽግግር ጉዳይ ላይ የተደረገው ውይይት ያለስምምነት ተጠናቀቀ
ከሳምንት በፊት መፈንቅለ መንግስት መደረጉን ተከትሎ የኢኮዋስ ልዑክ አባላት ለ3 ቀናት በማሊ ተወያይተዋል
የሽግግር መንግስት ጉዳይ በማሊያውያን እንደሚወሰን የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች አስታውቀዋል
በማሊ የሽግግር ጉዳይ ላይ የተደረገው ውይይት ያለስምምነት ተጠናቀቀ
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ወደ ማሊ የላከው ልዑክ አባላት ከሀገሪቱ ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት መሪዎች ጋር በመንግስታዊ ሽግግር ዙሪያ ያደረጉት ዉይይት ትናንት ያለ ስምምነት ተጠናቋል፡፡
በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የተመራው ልዑክ በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱት ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬይታ ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ለማደራደር ነበር ወደ ማሊ ያቀናው፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሩ በሽግግር ወቅት ሀገሪቱን ማን እስከመቼ ይምራ ወደሚል መቀየሩን የድርድሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
ይህ የሆነው ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን መውረዳቸውን እና ይህንም ያደረጉት መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት አካላት ሳያስገድዷቸው በራሳቸው ፈቃድ መሆኑን ለልዑኩ አባላት በማሳወቃቸው መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በሽግግሩ የመሳተፍም ሆነ ከዚህ በኋላ ወደ ፖለቲካ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ለጉድላክ ጆናታን መግለጻቸውም በዘገባው ተካቷል፡፡
ለአንድ ዓመት የሚቆይ የሽግግር ጊዜ ተግባራዊ እንዲደረግ በአማራጭነት ቢቀርብም ወታደራዊ መሪዎች ከምርጫ ይልቅ ሪፎርም መቅደም አለበት የሚል አቋም በመያዛቸው ስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡
የውይይቱን ያለስምምነት መጠናቀቅ ተከትሎ ኮሎኔል እስማኤል ዋጉ በሰጡት መግለጫ ዉይይቱን በተመለከተ አደራዳሪዎቹ ለየሀገራቱ መሪዎች ሪፖርት ገልጸው ፣ ነገር ግን የሽግግሩ አስተዳደር የመጨረሻ ውሳኔ በሀገርዉስጥ ድርድር እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡
“ምንም ነገር አልተወሰነም ፡፡ ሁሉም ሰው የየራሱን አመለካከት ነው የገለጸው፡፡ የሽግግሩ አወቃቀር የመጨረሻ ውሳኔ እዚሁ በኛ በማሊያውያን ይወሰናል” ብለዋል፡፡
ኢኮዋስ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ምርጫ ተካሂዶ የሪፎርሙ ስራ በሲቪል መንግስት ሊከናወን ይገባል የሚል አቋም ይዟል፡፡ በተቃራኒው በርካታ ተንታኞች በቅድሚያ ሪፎርም ተደርጎ ህዝቡን እና ወታደሮችን ለምሬት የዳረጉ እብደ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እልባት ሳያገኙ ምርጫ ማድረግ የከፋ መዘዝ ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
በማሊ ባለፈው ሳምንት ነበር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተካሒዶ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ በእስላማዊ ታጣቂዎች ከፍተኛ ስጋት በተደቀነባት ማሊ፣ እንደ ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ሁሉ ተጨማሪ የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡