ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን “ታሪክ ፖለቲካን ሳይሸፍን፤ፖለቲካ ደግሞ ታሪክን ሳያደቅ” የየራሳቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ምሁራን ተስማምተዋል
በኢትዮጵያ ፖለቲካና ታሪክ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንደሌለና ይህም በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዳይኖር ማድረጉን የታሪክ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡
የታሪክ ምሁራንና ጸሀፊዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት እንዲኖርና ታሪክ ፖለቲካን ሳይሸፍን፤ፖለቲካ ደግሞ ታሪክን ሳያደቅ የየራሳቸውን ሥራ ብቻ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን በታሪክና በፖለቲካ መካከል ቅራኔ መኖሩንና ይህም ሊፈታ እንደሚገባ ነው ምሁራን በተደጋጋሚ ከሰጡት ሀሳብ መረዳት የሚቻለው፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና የሕግ መምህሩ ዶ/ር አልማው ክፍሌ ፖለቲካ እና ታሪክ ጤናማ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸው አንዱ አንዱን ሳይጫን ሁለቱም ሚናቸውን ማሳየት መቻል አለባቸው ብለዋል፡፡
ዶ/ር አልማው ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ታሪክ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን ለብቻው የሚገባውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ገልጸው ታሪክ የፖለቲካን ሥራ መሥራት እንደሌለበት፤ ፖለቲካም የራሱን ሥራ መስራት እንጂ ታሪክን መቀማት እንደማይገባው ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አልማው ክፍሌ፡ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና የሕግ መምህር
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕ/ር አየለ በከሬ በበኩላቸው ፖለቲካ ጤናማ ከሆነ ሕዝብን ለማስተዳደር ፤ ሕዝብ በሀገሩ ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ ታሪክ እንደ መረጃና ማጣቀሻ እንደሚያገለግልና የአሁኑን ለመገንባት እንደሚረዳ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ከታሪክ ውስጥ ሕዝብን ሊቀሰቅስ የሚችል ቁንጽል ነገር ብቻ ተወስዶ ወደ ሕዝብ እንዲወርድ ሲደረግ ችግር እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡ ተባባሪ ፕ/ር አየለ በከሬ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሕዝብን ወደ አመጽ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ገልጸው የታሪክ እውነታዎችና ድርጊቶች ግን የግድ ወደ አመጽ ማምራት የለባቸውም ነው ያሉት፡፡
ተባባሪ ፕ/ር አየለ በከሬ፡ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር
ዶ/ር አልማው በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከታሪክና ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለ ገልጸው እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ የተጻፉ ጹሁፎች በተጓዥ፣ በገድል ጸሐፊና በልምድ ጸሐፊዎች የተጻፉ ታሪክ መሰል ጹሑፎች ናቸው ብለዋል፡፡ ጸሐፊዎቹ ሲጽፉ "የታሪክ ትምህርት እንዳልተማሩ" እና አንዳንዶቹ የመሰላቸውን እንደሚጽፉ ያነሱት ዶ/ር አልማው አብዛኞቹ ውዳሴ አይት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
“በሀገሪቱ ጎልቶ የተጻፈውና የታየው የፖለቲካ ታሪክ ነው” የሚሉት ዶ/ር አልማው ክፍሌ ኢኮኖሚ፣ እርሻ፣ኢንዱስትሪ፣ሕክምናና ሌሎቹም ታሪኮች መጻፍ እንደነበረባቸውና ወደፊትም ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተሰንደው መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
“ፖለቲካ ገንፍሎ ሌሎቹ ላይ ፈሷል” የሚሉት ዶ/ር አልማው እዚህ ሀገር የእርሻ ፤ስነጥበባት ፣ የወታደርና የሌሎች ጉዳዮች ታሪክ ሲጠየቅ አልተጻፈም ይላሉ፡፡ "ደርግ ስለሶሻሊዝም፣ ኢህአዴግ ደግሞ ስለብሔር ብሔረሰብ ጻፉ ሲሉ ስለነበር ታሪክ በትክክል ተጽፏል ማለት አይቻልም" ብለዋል፡፡ ታሪክ ከፖለቲካ ነጻ ሊሆን እንደማይችል ያነሱት ምሁራኑ ይሁንና ግን ግንኙነታቸውን ጤናማ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ፖለቲካ ለታሪክ ቦታውን መልቀቅና ታሪክ ሚናውን መጫወት እንዳለበትም ነው ምሁራኑ የተናገሩት፡፡
ፖለቲካ ታሪክን መርዳት አለበት ያሉት ምሁራኑ አሁን ላይ በተከታታይ ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው በዚህም ልዩነትን ማጥበብ ይቻላል ብለዋል፡፡ የታሪክ እውነታዎችና ድርጊቶች የግድ ወደ አመጽ ማምራት የለባቸውም ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ ተባባሪ ፕ/ር አየለ በከሬ ይህን ሲያስረዱ ፣ በ19 ኛው ክ/ዘመን ለተደረገ ድርጊት ይህኛው ትውልድ ኃላፊነት መውሰድ የለበትም ይላሉ፡፡
በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ብሔራዊ የማህበረሰብ ተኮር የምክከር መድረክ አካል የሆነው የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ፀሐፊያን የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ 60 የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ፀሐፊያን መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ዳይሬክተር ጄነራል መከለያ ባርጊቾ ፣ ምሁራኑ ለብሔራዊ መግባባት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች ላይ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው "ውይይቱ ችግሮችን ለመለየት ያስችላቸዋል" ብለዋል፡፡
መከለያ ባርጊቾ፡ በሰላም ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ዳይሬክተር ጄነራል
በቀጣይም ጎልተው በሚወጡ ችግሮች ላይ አብረው የጋራ መፍትሄ እንዲፈልጉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ትልልቅ ብሔራዊ ምክክሮች ቀጣይነት እንደሚኖራቸውም ነው ዳይሬክተር ጄነራሏ ለአል ዐይን ኒውስ የገለጹት፡፡