በኢትዮጵያ አምስት የተለያዩ ቦታዎች ዕምቅ የነዳጅ ሀብት እንዳለ ተገለጸ
ባለፉት 5 ወራት የማዕድን ዘርፉ ከታቀደው በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል ተብሏል
ኢትዮጵያ ለማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ጠ/ሚ ዐቢይ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ኢትዮጵያ እሴቶችን በመጨመር በየአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ ማዕድን አውጪዎችን እና ማህበረሰቦችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ፣ በርካታ የተፈጥሮ ማዕድናትን የታደለች ሀገር መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
ወርቅ፣ ቤዝ ብረቶች፣ ፖታሽ፣ ታንታሉም፣ ሰንፔር፣ ኤመራልድ እና ኦፓል ሀገሪቱ ካሏት ማዕድናት ወስጥ ጥቂቶቹ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለማምረት የሚያስችለንን ሀገራዊ ዐቅም በመፍጠር፣ የውጪ ገበያ እና የውጪ ምንዛሬ የማግኘት ዐቅማችንን እናጠናክራለን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፉ ክፍት መደረጉን ያነሱት ኢ/ር ታከለ ፣ በሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም እንዲቻል በዘርፉ ያሉ ሀብቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ የተደራጁ መረጃዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የማዕድን የአዋጭነት ጥናት የተደረገባቸው ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ንግድ የሚውሉ ሲሚንቶ፣ የከሰል ድንጋይ፣ ማዳበሪያ፣ ብረት፣ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ጀምስቶንና የነዳጅ ሀብት ለኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸውን ሚኒስትሩ ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚገኙ የማዕድንና የነዳጅ እምቅ ሀብቶች ጥናት የተደረገባቸው መሆኑንና ሁሉም በመረጃና በጥናት የተደገፉ መሆናቸው ሥራውን ቀልጣፋ እንደሚያደርግም ነው ኢ/ር ታከለ ኡማ ያብራሩት፡፡
ያልተነኩት የነዳጅና የጋዝ ሀብቶችን በተመለከተ ግልጽነት ለመፍጠርና ለኢንቨስትመንት በሚያመች መልኩ መረጃዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የፔትሮሊየም ፕላንና ልማት ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክተር ሰሎሞን ካሳ (ዶ/ር)፣ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን በሦስት ቦታዎች ፣ በጋምቤላ በአንድ ቦታ፣ በደቡብ ኦሞ በአንድ ቦታ፣ እንዲሁም በማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ዕምቅ የነዳጅ ሀብት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ቦታዎችን የያዘ የነዳጅ ሀብት መኖሩን አስረድተው፣ በዚህ ዘርፍ ባለሀብቶች መሰማራት ከፈለጉ ክፍት መሆኑን አስታቀዋል፡፡ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ክፍት መደረጉን ኢ/ር ታከለ ኡማም ገልጸዋል፡፡
በማዕድንና ነዳጅ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች በጨረታ፣ እንዲሁም በዘርፉ የነበራቸው ተሳትፎና ታማኝነት፣ ያስመዘገቡት ካፒታል ትክክለኛ መሆኑ ከታመነበት ዕድሉ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡
ለጨረታ ክፍት የተደረጉት የማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ፕሮጀክቶቹ በቅርብ ጊዜ ለዓለም አቀፍ ጨረታ ክፍት ይደረጋሉም ተብሏል፡፡
በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በማዕድን ማምረትና ተቋማትምርምር ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ የ 63 ተቋማት ፈቃድ መሰረዙ ይታወሳል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባለፉት አምስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ የማዕድን ዘርፉ ከታቀደው በላይ 271 በመቶ ማስመዝገቡን በቅርቡ መግለጻቸው የሚታወቅ ነው፡፡