አባ ፍራንሲስ “የሚያስከፋ እስካልሆነ ድረስ ስለ ፈጣሪ መቀለድ ችግር የለውም” አሉ
የሮማው ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ ኮሜዲያን ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል
አባ ፍራንሲስ ለኮሜዲያኑ "በፈጣሪ ላይ እንኳን መሳቅ ትችላላችሁ፣ ይህ መናፍቅነት አይደለም” ብለዋል
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ “የሚያስከፋ እስካልሆነ ድረስ ስለ ፈጣሪ መቀለድ ችግር የለውም” አሉ።
አባ ፍራንሲስ ከመላው ዓለም ከተውጣጡ ከ100 በላይ ኮሜዲያን፣ የፊልም ተዋናዮች እና ጸሃፊዎችን በትናንትናው እለት በቫቲካን አግኝተው አነጋግረዋል።
ከአባ ፍራንሲስ ጋር ከተገናኙ ታዋቂ ሰዎች መካከልም የአሜሪካ ታዋቂው የሾው ቢዝ አቅራቢ ውሁፒ ግልድበርግ፣ ጂሚ ፋሎን፣ ካነን ኦበሪየን፣ ክሪስ ሮክ እና ስቴፈን ኮልበርት እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚሁ ወቅት በጣሊያንኛ ንግግር ያደረጉት አባ ፍራንሲስ "በፈጣሪ ላይም መሳቅ እችላለን” ያሉ ሲሆን፤ ይህ ስድብ አይደለም እኛ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር እንደምንጫወት እና እንደቀልድ ሁሉ በፈጣሪ ላይም እንችላለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
“የሚያስከፋ እስካልሆነ ድረስ ስለ ፈጣሪ መቀለድ ችግር የለውም” ያሉት አባ ፍራንሲስ፣ “እያልኩ ያለሁት ነገር መናፍቅነት አይደለም፤ በአንድ ሰው ከንፈር ላይ እንዴት ፈገግታን መፍጠር እንዳለብህ ካወክ እና አንድን ሰው ፈገግ ካሰኝህ፤ እግዚአብሄርም እንዲስቅ ታደርጋለህ” ብለዋል።
የሮማው ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ 30 ደቂቃ ከፈጀው እና ከመስመር ወጣ ያለ ነው የተባለውን ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከኮሜዲያኖቹ ጋር እየተጨባበጡ ተቀላልቀደዋል።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው ለየት ባሉ እና አነጋጋሪ አስተያየታቸው ይታወቃሉ።
አባ ፍራንሲስ ከቀናት በፊት ቄሶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በተቻለ መጠን አጭር እንዲያደርጉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አባ ፍራንሲስ አክለውም ለማስቀደስ እና ሌሎች በረከቶችን ለማግኘት ብለው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ የዕምነቱ ተከታዮች በቄሶች አገልግሎት መርዘም ምክንያት እንቅልፍ እየጣላቸው ነው ብለዋል።
ቄሶች ስለ ጌታ ከመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ለምዕመናን የሚያስተምሩበት ጊዜ ከስምንት ደቂቃ መብለጥ የለበትም ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ ተናግረዋል።