አባ ፍራንሲስ ቄሶች ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሰበካ እንዳያደርጉ ከለከሉ
ቄሶች የወንጌል ሰበካቸው በመርዘሙ ምክንት ምዕመናን እንቅልፍ እየጣላቸው ነው ብለዋል
ቄሶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጡ ተከታዮች ስለ ጌታ ቃል የሚናገሩበት ጊዜ ከስምንት ደቂቃ መብለጥ እንደሌለበት አባ ፍራንሲስ ተናግረዋል
አባ ፍራንሲስ ቄሶች ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሰበካ እንዳያደርጉ ከለከሉ፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ቄሶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በተቻለ መጠን አጭር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
አባ ፍራንሲስ አክለውም ለማስቀደስ እና ሌሎች በረከቶችን ለማግኘት ብለው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ የዕምነቱ ተከታዮች በቄሶች አገልግሎት መርዘም ምክንያት እንቅልፍ እየጣላቸው ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቄሶች የጌታን ቃል ለተከታዮች በሚያስተምሩበት ወቅት የምዕመናኑን ስሜት ሊረዱ ይገባል ያሉት አባ ፍራንሲስ ቄሶች በተቻለ መጠን አግልገሎቶቻቸውን አጭር እንዲያደርጉ ማለታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ቄሶች ስለ ጌታ ከመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ለምዕመናን የሚያስተምሩበት ጊዜ ከስምንት ደቂቃ መብለጥ የለበትም ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ ተናግረዋል፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ አሁኑኑ እንዲሞቱ የጸለዩ ቄሶች ይቅርታ ጠየቁ
“የወንጌል ሰበካው ከስምንት ደቂቃ የማይበልጥ ከሆነ ምዕመናኑ እንቅልፍ አይወስዳቸውም፣ ቄሶች ይህንን ሊረዱ ይገባል” ማለታውም ተገልጿል፡፡
የ87 ዓመቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ አክለውም “ቄሶች ብዙ ማውራት የለባችሁም፣ የምታወሩት ከረዘመ የሚያዳምጣችሁ አይኖርም” ብለዋል፡፡
ከሁለት ወር በፊት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቄሶች ናቸው የተባሉ ቄሶች በቡድን አባ ፍራንሲስ እንዲሞቱ ሲጸልዩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ከተጋራ በኋላ ብዙ ተመልካች ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
ብዙዎች የቄሶቹን ድርጊት ኮንነው አስተያየት የሰጡ ሲሆን ቀሪዎች ደግሞ ጉዳዩን በመዝናኛነት እንደተመለከቱት በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡
በስፓኒሽ ቋንቋ ጸልየዋል የተባሉት እነዚህ ቄሶች ጸሎታቸው በበይነ መረብ ቀጥታ የተላለፈ ሲሆን አንድ ቄስ “አሁን ደሞ ፖፕ ፍራንሲስ አሁኑኑ ወደ ገነት እንዲሄዱ እጸልያለሁ” ሲሉ አብረው የነበሩ ሁሉም ቄሶች ሲስቁ ታይተዋል፡፡
እነዚህ በአባ ፍራንሲስ ላይ ተሳልቀዋል የተባሉ ቄሶች በመጨረሻም በይፋ ይቅርታ እንደጠየቁ ተገልጿል፡፡