ርእሰ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ እስራኤልና ፍልስጤም ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳሰቡ
አባ ፍራንሲስ በእየሩሳሌም የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃትና በቀጠለው የዌስት ባንክ ግጭት ለመፍታት ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እየጨመረ ያለው የኃይል እርምጃም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል
የሮማ ካቶሊካውያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናት በቅርቡ በእየሩሳሌም የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት እና በቀጠለው የዌስት ባንክ ግጭት ተከትሎ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ እሁድ በሰጡት ቡራኬ ሁከት ለሁለቱም ሀገራት “መጪውን ጊዜ እየገደለ ነው” ብለዋል።
ባለፈው ረቡዕ በእየሩሳሌም ወጣ ብሎ በሚገኙ አውቶቡስ ማቆሚያ ሁለት ቦምብ ፈንድቶ አንድ የ16 ዓመት ልጅ ህይወቱ ሲያልፍ በትንሹ 14 ሰዎች ቆስለዋል። ጠቃቱንም የፍልስጤም ታጣቂዎች የፈጸሙት ነው ተብሏል።
- የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፤ የሮማ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ፑቲንና ባይደን እንዲያሸማግሉ ጠየቁ
- ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ፤ “ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን ማቅረብ በሞራል ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነው” አሉ
ማክሰኞ ምሽት አንድ የ16 አመቱ ፍልስጤማዊ ልጅ በእስራኤላውያን በተያዘው የዌስት ባንክ ናቡልስ ከተማ በተፈጠረ ግጭት በእስራኤል ወታደሮች በጥይት ተመትቶ መገደሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሁለቱንም ክስተቶች ጠቅሰው እየሩሳሌም የደረሰውን ፍንዳታ “አሳፋሪ” ሲሉ ገልጸውታል። ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እየጨመረ ያለው የኃይል እርምጃም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
"ሁከት መጪውን ጊዜ ይገድላል፤ የታናናሾችን ህይወት ያቋርጣል እና የሰላም ተስፋንም ያዳክማል፤ ለእነዚህ ለሞቱት ወጣቶች እና ለቤተሰቦቻቸው በተለይም ለእናቶቻቸው እንፀልይላቸው" ሲሉ በአስር ሽህዎች ለተሰባሰቡ ሰዎች ተናግረዋል።
የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናት የውይይት ፍለጋውን በላቀ መንገድ እንዲወስዱት ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ፤ ሀገራቱ እርስ በርስ መተማመንን መገንባት አለባቸው ብለዋል።
ይህ ካልሆነ “በቅድስቲቷ ሀገር ውስጥ ለሰላም መፍትሄ መቼም አይመጣም” ብለዋል።