የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፤ የሮማ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ፑቲንና ባይደን እንዲያሸማግሉ ጠየቁ
ፕሬዝዳንት ማክሮን የዩክሬን ቀውስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ከሚያደርጉ መሪዎች አንዱ ናቸው
ማክሮን፤ "ሊቀ ጳጳሱ በጆ ባይደን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ" የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን፤ የሮማው ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በየክሬን ቀውስ ጉዳይ ፑቲን እና ባይደንን እንዲያሸማግሉ ጠየቁ።
እንደ ፈረንሳዩ ለ ፖይንት ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ፕሬዝዳንት ማክሮን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ሁለቱም መሪዎች እንዲያነጋግሩ የጠየቁት በሮም ከጳጳሱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
ማክሮን ያቀረቡት ጥያቄ በዩክሬን ውስጥ ያለውን "የሰላም ሂደት ለማጠናከር" በሚያስችል መልኩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለፑቲን፣ ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ኪሪል እና ባይደን ጥሪ እንዲያደርጉ የሚል መሆኑ የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።
"ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ቭላድሚር ፑቲንን እና የሞስኮውን ፓትርያርክ ኪሪልን እንዲሁም ጆ ባይደንን እንዲያነጋግሩ አበረታታለሁም ነው ያሉት ማክሮን።
በዩክሬን ያለውን የሰላም ሂደት እንዲሳካ አሜሪካ በጠረጴዛ ዙሪያ እንድትቀመጥ እንፈልጋለን ሲሉም አክለዋል።
በመቀጠልም "ጳጳሱ በጆ ባይደን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ" የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል።
ማክሮን በባይደን እና በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ እውነተኛ መተማመን እንዳለ እርግጠኛ መሆናቸው የተናገሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት፤ በሄይቲ እና በዩክሬን የነበረው የአሜሪካን ተሳትፎ ወደነበረበት እንዲመለስ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉም ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በተካሄደው የሰላም ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ወደ ፓሪስ ተመልሰዋል።
የሩስያ ወታደራዊ ዘመቻ በዩክሬን መጀመሩን ተከትሎ ቀውሱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በማሰብ ከፑቲን ጋር ግልጽ ግንኙነት ካደረጉ ጥቂት የአውሮፓ መሪዎች መካከል ማክሮን አንዱ መሆናቸው ይታወቃል።