ቱርክ በሰሜን ሶሪያ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች ተገደሉ
ቱርክ ጥቃቱ የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ እና የሶሪያ ኩርድ ታጣቂዎች የጦር ሰፈሮች ላይ ያነጣጠረ ነው ብላለች
ቱርክ ከአንድ ሳምንት በፊት ስድስት ሰዎች ለሞቱበት እና ከ80 በላይ ለቆሰሉበት ጥቃት አጻፋ እየሰጠች ነው
የቱርክ አውሮፕላኖች በሰሜናዊ ሶሪያ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ሁለት መንደሮች ድብደባ መፈፀማቸው ተነግሯል።
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንደገለጸው 12 የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችና የሶሪያ መንግስት ጦር አባላት በቱርክ ተገድለዋል፡፡
የቱርክ መከላከያ ሚንስቴር ሪፖርቶቹን አረጋግጦ ጥቃቱ ያነጣጠረው የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ እና የሶሪያ ኩርድ ታጣቂዎ የጦር ሰፈሮች ላይ ነው ማለቱን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ሚንስቴሩ በትዊተር ገፁ "የአሸባሪዎች መፈንጫ ስፍራ በድብደባ ኢላማ ሲደረግ" በማለት አንካራ የወሰደችውን ጥቃት ገልጿል።
ቱርክ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢስታንቡል የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ በኢራቅ በሚገኘው የኩርድ ታጣቂ ላይ ድንበር ተሻጋሪ ዘመቻ ካጠናቀቀች በኋላ በሰሜን ሶሪያ ያነጣጠረ እቅዷን ይፋ አድርጋለች።
በኢስታንቡል ኢስቲካል ጎዳና ከአንድ ሳምንት በፊት ስድስት ሰዎች ለሞቱበት እና ከ80 በላይ ለቆሰሉበት ጥቃት መንግስት የኩርድ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
እስካሁን ምንም አይነት ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነት ባይወስድም፤ የኩርድ ታጣቂዎችና የሰራተኞች ፓርቲ ግን እጃችን የለበትም ሲሉ አስተባብለዋል።
ቱርክ ስለ ተልዕኮው ዝርዝር መረጃ ባትሰጥም፣ የኩርድ ኃይሎች በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የሚገኘው ኮባኔ የተባለ ስፍራ በቱርክ ወረራ ተመቷል ብለዋል።
ሲጂቲኤን እንደዘገበው ተርኪዬ በሰሜን ሶሪያ በኩርድ ሚሊሻ ላይ እስካሁን ሦስት ዘመቻዎችን አድርጋለች። ፕሬዝዳንት ረሲጽ ጣይብ ኤርዶጋን ቀደም ሲል ተርኪዬ ላይ ሌላ ዘመቻ ልታደርግ እንደምትችል ጠቁመው ነበር።