የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች “ቪኤአር” ጥቅም ላይ መዋሉ እንዲቀጥል ተስማሙ
ወልቭስ ያቀረበው ቴክኖሎጂው በቀጣዩ የውድድር አመት ይታገድ ጥያቄ በ19 ክለቦች ተቃውሞ ውድቅ ተደርጓል
በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቪኤአር) የእግርኳስን ተፈጥሯዊ ውበት እያደበዘዘ ነው የሚል ቅሬታ ይቀርብበታል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የ”ቪኤአር” ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉ እንዲቀጥል ተስማሙ።
የሊጉ ክለቦች እያካሄዱት ባለው አመታዊ ጉባኤ ነው ቴክኖሎጆጂው በ2024/25 የውድድር አመትም ጥቅም ላይ እንዲውል የተስማሙት።
ወልቭስ ባለፈው ግንቦት ወር በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቪኤአር) እንዲታገድ ባቀረበው ጥያቄ ዙሪያ ክለቦች ድምጽ እንዲሰጡ ተደርጎ 19ኙ (ከወልቭስ ውጭ ያሉት) ክለቦች ተቃውመውታል።
የወልቭስ ጥያቄ ተቀባይነት ኖሮት በቀጣዩ አመት ቴክኖሎጂው እንዲታገድ 14 ክለቦች ድጋፍ መስጠት ነበረባቸው።
በአውሮፓ ተወዳጁ ሊግ በ2019/2020 የውድድር አመት ያስጀመረው “ቪኤአር” በደጋፊዎችና ክለቦች ትችት ማስተናገድ ከጀመረ ሰነባብቷል።
ቴክኖሎጂው በተለይ ጎል ከተቆጠረ በኋላ ስሜትን ከመግለጽ አንጻር የተጫዋቾችን ስነልቦና እየጎዳ መሆኑን የተለያዩ ክለቦች እና ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል።
በዳኞች የተላለፉ ውሳኔዎች አጠራጣሪ ሆነው በ”ቪኤአር” ሲታይ የሚወስደው ረጅም ጊዜም ተወዳጁን እግርኳስ ተፈጥሯዊ ውበት እየቀነሰው መሄዱንም የሚያነሱት ቀላል አይደሉም።
ቴክኖሎጂው ሜዳ ውስጥ ያሉትን ዳኞች ተአማኒነት እና ተቀባይነትም ጥያቄ ውስጥ መክተት መጀመሩና ዳኞችም ጭምር በአንዳንድ የቪኤአር ውሳኔዎች ላይ ደስተኛ አለመሆናቸውን መናገራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ዛሬ ቴክኖሎጂው እንዲቀጥል ድምጻቸውን ቢሰጡም ከወልቭስ ባሻገር የተለያዩ ክለቦች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
በመስከረም ወር የሊቨርፑሉ ልዊስ ዲያዝ በቶተንሃም ላይ ያስቆጠራት ጎል ከጨዋታ ውጭ ናት በሚል የተላለፈው አከራካሪ የቪኤአር ውሳኔ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ኖቲንግሀም ፎረስትም ከኤቨርተን ጋር ሲጫወት ሶስት የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄዎችን መከልከሉን ማሳወቁና በቴክኖሎጂው ላይ ቅሬታውን ማቅረቡ አይዘነጋም።
ሊቨርፑልም ሆነ ኖቲንግሃም ፎረስት በዛሬው የሊጉ አመታዊ ጉባኤ ቴክኖሎጂው እንዲቀጥል መስማማታቸው ግን የወልቭስን ድካም ከንቱ አድርጎታል ተብሏል።
ስዊድን ባለፈው ወር ቪኤአር ጥቅም ላይ እንዳይውል በማገድ ከ30 የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አባላት ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።
ስቶኮልም ከዚህ ውሳኔ ለመድረሷም በቪኤአር ውሳኔ ምክንያት ደጋፊዎች ግጭት ውስጥ መግባታቸው በምክንያትነት ተጠቅሶ ነበር።