ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግብ በማስቆጠር ሁለት አዳዲስ ክብረወሰኖችን ሰበረ
ሮናልዶ በ4 ሊጎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የዓለማችን የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል
የ39 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ዘመኑ ያስቆጠራቸው ግቦች 893 ደርሰዋል
የ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳሱ ዓለም አሁንም አዳዲስ ክብረወሰኖችን ማስመዝገቡን እና መስበሩን ቀጥሎበታል።
ለሳዑዲ አረቢያው አል ናሰር የሚጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የዘንዶሮ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን፤ በ31 ጨዋታ 35 ጎሎች መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
ሮናልዶ ክለቡ አል ናሰር በትናንትናው እለት አል ኢትሃድን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ሁለት ጎሎች ማስቆጠሩን ተከትሎ ነው በውድድር ዓመቱ በሳዑዲ ሊግ ያስቆጠራውን ግብ መጠን 35 ያደረሰው።
በዚህ ሮናልዶ በሳውዲ ሊግ በአንድ የውድድር አመት ብዙ ጎል በማስቆጠር አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
ሮናልዶ በፈረንቹ 2019/20 በሞሮኳዊው ተጫዋች በ34 ግብ ተይዞ የነበረው የአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረወሰንን በእጁ አስገብቷል።
ይህንን ተከትሎም ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ4 የተለያዩ ሊጎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ የመጀመሪያው ታሪካዊ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
ሮናልዶ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ በስፔን ላሊጋ እና በጣሊያን ሴሪ ኤ ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆን የቻለ ሲሆን፤ አራተኛውን ደግሞ በሳዑዲ ፕሮ ሊግ አሳክቷል።
የክርስቲያኖ ሮናልዶ ከፍተኛ ግብ አግቢነት ታሪክ የጀመረው በእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናትድ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2007/08 የወድድር ዓመት በ38 ጨዋታዎች 31 ግብ በማስቆጠር የወርቅ ጫማ መሸለሙም ይታወሳል።
ሮናልዶ በመቀጠልም በስፔን ላሊጋ በ9 ዓመት ቆይታው ከተፎካካሪው ሊዮኔል ሜሲ ጋር እየተቀያየረ 3 የውድድር ዓመታትን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል።
በመቀጠል ወደ ጣሊያን ያቀናው ሮናልዶ በጁቬንቱስ ቆይታውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን የቻለ ሲሆን፤ በአንድ የውድድር ዘመን በ33 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 29 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ዘመኑ ያስቆጠራው ግቦች ቁጥርም 893 መድረሳቸው ነው የተገለጸው።
ሮናልዶ ከፍተኛ ጎሉን ለሪያል ማድሪድ ያስቆረ ሲሆን፤ ለማንቸስተር ዩናትድ ያስቆጠራቸው ግቦች ሁለተኛ ላይ ነው።