ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሶስት ቀናት በኋላ ይጀመራል
በክረምቱ የዝውውር መስኮት የትኛው ክለብ በርካታ ተጫዋቾችን አስፈረመ? የትኛውስ ዋንጫ የማንሳት እድሉ ከፍተኛ ነው ተባለ?
በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ለተጫዋች ዝውውር ከ1 ቢሊየን ፓውንድ በላይ ወጪ ተደርጓል
የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን አርብ ይጀመራል።
ባለፈው የውድድር አመት የሶስትዮሽ ዋንጫ ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ በተርፍ ሞር በርንሌይን ምሽት 4 ስአት በመግጠም ውድድሩን በይፋ ያስጀምራል።
ለ248 ቀናት ሳይሸነፍ ፕሪሚየር ሊጉን ለማንሳት ተቃርቦ የነበረው አርሰናል ደግሞ ቅዳሜ 8 ስአት ከ30 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስትን ያስተናግዳል።
እሁድ 12 ስአት ከ30 በስታንፎርድ ብሪጅ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታም የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ ሰኞ ምሽት 4 ስአት ላይ በኦልትራፎርድ ወልቭስን ይገጥማል።
የእንግሊዝ ክለቦች በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስካሁን ከ1 ቢሊየን ፓውንድ በላይ ለተጫዋቾች ዝውውር አውጥተዋል።
አርሰናል በዚህ የዝውውር መስኮት 203 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ በማውጣት ቀዳሚው ክለብ ነው።
መድፈኞቹ ለዴክላን ራይስ ዝውውር 105 ሚሊየን ፓውንድ ያወጡ ሲሆን፥ ጁሪን ቴምበር ከአያክስ እንዲሁም ካይ ሃቨርትዝን ደግሞ ከቼልሲ በውድ ዋጋ አስፈርመዋል።
እስካሁን 163 ነጥብ 1 ሚሊየን ፓውንድ ለተጫዋቾች ዝውውር ያወጣው ማንቸስተር ዩናይትድም በውድድር ዘመኑ ተፎካካሪ ሆኖ ለመምጣት ጥረት እያደረገ ነው።
የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም፣ አስቶንቪላ እና በርንማውዝም ለተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ወጪ ካወጡት ክለቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ለአርሰናል ዴክላን ራይስን የሸጠው ዌስትሃም እና ኤቨርተን ተጫዋቾችን ለማዛወር እስካሁን ምንም ወጪ ያላወጡ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች መሆናቸውንም የቶክ ስፖርት መረጃ ያሳያል።
ጎል ስፖርት ድረገጽ ደግሞ በ2023/24 እስከ 5ኛ ደረጃን ይዘው የማጠናቀቅ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸውን ክለቦች ይፋ አድርጓል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስካሁን 102 ነጥብ 6 ሚሊየን ፓውንድ ያወጣው ማንቸስተር ሲቲ በዚህኛው የውድድር አመትም ለሻምፒዮንነት ግምት የሚሰጠው ነው ይላል ዘገባው።
የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ማቲዮ ኮቫቺችን ከቼልሲ፤ ጆስኮ ቫርዲዮልን ከአርቢ ላይፕዚሽ ያስፈረመ ሲሆን፥ ኢካይ ጉንዶጋን እና ሪያድ ማህሬዝን ሸኝቷል።
ካይል ወከር እና ጃኦ ካንሴሎን ጨምሮ ከሶስት በላይ ተጫዋቾችም የዝውውር መስኮቱ ሳይጠናቀቅ ክለቡን እንደሚለቁ የሚጠበቅ ቢሆንም ሲቲ ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ተጫዋቾችን ያዛወረው አርሰናል፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ በደረጃ ሰንጠረዡ እስከ 5ኛ ደረጃን ይዘው እንደሚያጠናቅቁ ጎል ስፖርት በድረገጹ ግምቱን አስቀምጧል።