የቶትንሀሙ ሀሪ ኪን፣ የዌስትሀሙ ዲክላን ራይስ፣ የሌይስተር ሲቲው ጀምስ ማዲሰን የዘንድሮው የክረምት ዝውውር ዋነኛ ኢላማ ተጫዋቾች ሆነዋል
እንግሊዛውያን ተጫዋቾች በዘንድሮው የክረምት ዝውውር በብዙ ክለቦች ተፈላጊ ሆነዋል።
ከተጀመረ 28ኛ ቀኑ ላይ የሚገኘው የዘንድሮው የክረምት ተጫዋች ዝውውር እንግሊዛውያን የበለጠ ደምቀውበታል።
የቦሪሲያ ዶርትሙንዱ እንግሊዛዊው ቤልንጊሀም ለሪያል ማድሪድ በመፈረም የተጀመረው ይህ የዝውውር ጊዜ እንደቀጠለ ነው።
ሌሎቹ እንግሊዛውያን ተጫዋቾች የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦችን ትኩረት የሳቡ ሲሆን የቶትንሀሙ አጥቂ ሀሪኬን፣ የዌስትሀሙ የአማካኝ ስፍራ ተጫዋች ዲክላን ራይስ፣ የሌይስተሩ ጄምስ ማዲሰን በዘንድሮው የክረምት የዝውውር ወቅት አድማቂ ሆነዋል።
በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ውድድሩን ለረጅም ሳምንታት ሲመራ ቆይቶ ዋንጫውን በማንችስተር ሲቲ የተነጠቀው አርሰናል የዲክላን ራይስ ዋነኛ ፈላጊ ክለብ ሆኗል።
ተቀናቃኙ ማንችስተር ሲቲም ሌላኛው የዲክላን ራይስ ፈላጊ የሆነ ሲሆን ተጫዋቹን ለማስፈረም ያቀረበው 70 ሚሊዮን ዩሮ በተጨዋቹ ባለቤት በዌስትሀም ክለብ ውድቅ መደረጉን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል።
አርሰናል በበኩሉ ለሶስተኛ ጊዜ ራይስን የግሉ ለማድረግ 105 ሚሊዮን ዩሮ ለዌስትሀም ያቀረበ ሲሆን ክለቡ እስካሁን የመድፈኞቹን ጥያቄ ስለመቀበሉ አልያም ውድቅ ስለማድረጉ ምላሽ አልሰጠም።
ቶማስ ፓርቴይን ለሳውዲ ክለቦች ለመሸጥ ፍላጎት ያለው አርሰናል ዲክላን ራይስን የራሱ ማድረጉን እስከሚያረጋግጥ ግን ሽያጩን ማዘግየትን መርጧል።
ዌስትሀም የአርሰናልን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ ማንችስተር ሲቲ አዲስ እና የተሻለ የዝውውር ሂሳብ ለራይስ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
የቶትንሀም የምንግዜም አጥቂ ሀሪኬን ወደ ጀርመኑ ባየርን ሙኒክ ሊያቀና እንደሚችል ተገልጿል።
ተጫዋቹ ከሙኒክ ጋር በደመወዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች መስማማቱ ሲገለጽ የቶትንሀም ውሳኔ በመጠበቅ ላይ ነውም ተብሏል።
ወደ ታችኛው ሊግ የወረደው ሌላኛው የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለብ ሌይስተር ሲቲ የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ጀምስ ማዲሰን በብዙ ክለቦች እየተፈለገ ነው።
የተጫዋቹ የረጅም ጊዜ ፈላጊ የሆነው ኒውካስትል ዩናይትድ እና ቶትንሀም ዋነኛ ፋለጊ ሆነዋል።
ቶትንሀም ለተጫዋቹ 40 ሚሊዮን ፓውንድ አቅርቧል የተባለ ሲሆን ኒውካስትልብዩናይትድ ተጫዋቹ የተሰጠው ዋጋ ተጋኗል የሚል አስተያየት አላቸው ተብሏል።
የሳውዲ አረቢያ ክለቦች ከበርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለብ ተጫዎቾችን በአማላይ ደመወዝ ለማስፈረም ጥረታቸው እንደቀጠሉ ተገልጿል።