ኪሊያን ምባፔም ከአልሂላል ክብረወሰን የሆነ የዝውውር ክፍያ ቀርቦለታል
የ5 ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለፈው አመት ጥር ወር ከማንቸስተር ወደ አል ናስር መዘዋወሩ የሳኡዲ ሊግ አለማቀፍ ትኩረትን እንዲስብ አድርጓል።
ፖርቹጋላዊውን ኮከብ ተከትለውም በርካታ ተጫዋቾች ለተለያዩ የሳኡዲ ክለቦች ፈርመዋል።
የሪያድ ክለቦች የሚያቀርቡት አማላይ የዝውውር ገንዘብም ታዋቂ ተጫዋቾችን ጭምር ወደ ሳኡዲ ማስኮብለሉን ቀጥሏል።
ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔም ከአል ሂላል በቀረበለት ክብረወሰን የሆነ ዝውውር ጉዳይ እንዲነጋገር ክለቡ ፒኤስጂ ፈቅዶለታል።
በዚህ የዝውውር መስኮት የሳኡዲን ክለቦች ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፦
ካሪም ቤንዜማ - ከሪያል ማድሪድ ወደ አል ኢትሃድ
የሪያል ማድሪድ ሁለተኛው ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ካሪም ቤንዜማ በነጻ ዝውውር የሳኡዲውን አል ኢትሃድ ተቀላቅሏል።
የ35 አመቱ ተጫዋች ለሁለት አመት የሚያቆይ ውል የተፈራረመ ሲሆን፥ በአመት 213 ሚሊየን ዶላር ያገኛል ተብሏል።
ንጎሎ ካንቴ - ከቼልሲ ወደ አል ኢትሃድ
በቼልሲ በቆየባቸው ሰባት አመታት የሻምፒዮንስ ሊግ እና ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ንጎሎ ካንቴ በጂዳ ከቤንዜማ ጋር ይጣመራል።
አል ኢትሃድ ለፈረንሳዊው ተጫዋች በአመት 109 ሚሊየን ዶላር እንደሚከፍል ስካይ ኒውስ አስነብቧል።
ጆታ - ከሴልቲክ ወደ አል ኢትሃድ
የ24 አመቱ ፖርቹጋላዊ ጆታ በስኮትላንዱ ክለብ ሴልቲክ ድንቅ ሁለት የውድድር አመታትን አሳልፏል።
ጆታ በ31 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ወደ አል ኢትሃድ የተዛወረ ሲሆን፥ ለሶስት አመት የሚይቆይ ውልም መፈረሙን የስኮትላንድ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ሩበን ኔቬስ - ከወልቭስ ወደ አል ሂላል
የ26 አመቱ ኔቬስ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ተሰናብተው ሳኡዲ ከገቡ ተስፈኛ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
ፖርቹጋላዊው አማካይ በአል ሂላል ለሶስት አመት የሚያቆየውን ውል የፈረመ ሲሆን፥ በአመት 60 ሚሊየን ዶላር ይከፈለዋል ተብሏል።
ካሊዱ ኩሉባሊ - ከቼልሲ ወደ አል ሂላል
ሴኔጋላዊው ተከላካይ ስታንፎርድ ብሪጅን ለቆ ወደ ሪያዱ ክለብ አል ሂላል ተቀላቅሏል።
ኩሉባሊ በ21 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ወደ ሳኡዲው ክለብ መዛወሩም ተዘግቧል።
ሰርጌ ሚሊንኮቪች - ከላዚዮ ወደ አል ሂላል
የ28 አመቱ ሰርቢያዊው አማካይ ሚሊንኮቪች በአል ሂላል እስከ 2026 የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።
አል ሂላል ለተጫዋቹ 44 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር እንደሚከፍልም ነው የተነገረው።
ኤድዋርድ ሜንዲ - ከቼልሲ ወደ አል አህሊ
በስታንፎርድ ብሪጅ ለሶስት የውድድር አመት የተጫወተው ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ ወደ ጂዳ አቅንቷል።
አል አህሊ ለ31 አመቱ ግብ ጠባቂ 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ይከፍላል።
ሮቤርቶ ፊርሚኖ - ከሊቨርፑል ወደ አል አህሊ
በቀያዮቹ ቤት ለስምንት አመት የቆየው ብራዚላዊው አጥቂ ፊርሚኖም ሜንዲን ተከትሎ አል አህሊን ተቀላቅሏል። በ2015 ከጀርመኑ ክለብ ሆፈኔም የመርሲሳይዱን ክለብ የተቀላቀለው ፊርሚኖ ከቀያዮቹ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ዋንጫዋችን አሳክቷል።
ሪያድ ማህሬዝ - ከማንቸስተር ሲቲ ወደ አል አህሊ
በ2022/23 ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ሶስትዮሽ ዋንጫ ያሳካው ማህሬዝ በጂዳ ከፊርሚኖ ጋር ለመጣመር ተስማምቷል።
ሁለቱ ክለቦች በአልጀሪያዊው ተጫዋች ዝውውር ዙሪያ ሲነታረኩ ቢቆዩም የ32 አመቱ ተጫዋች ለአል አህሊ የሶስት አመት ውል ፈርሟል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የሚጫወትበት አል ናስርም ማርሴሎ ብሮዞቪችን ከኢንተር ሚላን፤ ሴኮ ፎፋናን ከፈረንሳዩ ሎንስ እንዲሁም አሌክስ ቴሊስን ከማንቸስተር ዩናይትድ አስፈርሟል።
የሳኡዲ ክለቦች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊትም ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያዛውሩ ይጠበቃል።