ፕሬዘዳንት ባይደን ከቻይናው ዢ ጅንፒንግ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ተወያዩ
ባይደን ቻይና በሆንግኮንግ የምታደርገው የመብት ረገጣ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል
ፕሬዘዳንት ዢ በሆንግኮንግ፣በዢንጂያንግና በታይዋን ጉዳይ የሉአላዊነት ጉዳይ ስለሆነ አሜሪካ በጥንቃቄ ማየት እንዳለባት ለባይደን ገልጸውላቸዋል
የአሜሪካና ቻይና ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ባለበት ወቅት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፐንግ ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅት ባይደን ነፃ የኢንዶ ፓስፊክ ቀጣና ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ሲገልጹ ዢ ጅፒንግ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መፋጠጥ ለሁለቱም ሀገራት “አጥፊ” ነው ብለዋል፡፡ ባይደን ቻይና በሆንግኮንግ የምታደርገውን የመብት ረገጣ፣የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችና በታይዋን ላይ እየወሰደች ያለው ተግባር እንደሚያሳስባቸው አስምረው ተናግረዋል፡፡
የቻይናን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው የቻይናው ዢ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መፋጠጥ አደገኛ ነው፤ ሁለቱም ወገኖች መፈራረጅን ማቆም አለባቸው ብለዋል፡፡የስልክ ለውውጡ የተካሄደው በአሜሪካ ሰአት ረብእ ጠዋት ሲሆን በቻይና ሀሙስ ጠዋት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በስልክ ውይይቱ በሆንግኮንግ፣በዢንጂያንግና በታይዋን ጉዳይ ጠንካራ አቋም ያራመዱት ዢ፣ለባይደን ጉዳዩ የሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ጉዳይ ስለሆነ አሜሪካም በጥንቃቄ ማየት እንዳለባት ገልጸውላቸዋል፡፡ ቻይና የእሷ እንደሆነ በምትገልጸው በዲሞክራቲክ ደሴት አቅራቢያ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ የምትቃወመው ታይዋን፤ ባይደን ስጋታቸውን ስለገለጹ አመስግናለች፡፡
የዢና የባይደን ስልክ ውይይት የቻይና ባለስልጣናት ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው አመት መጋቢት ካወሩ በኃላ የመጀመሪያ ነው፡፡ ከእዚያ ወዲህ ፕሬዘዳንት ትራምፕ ለኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ቻይናን ከወቀሱ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡
ባለፈው ህዳር ዢ ጅንፒንግ ለባይደን የእንኳን ደስ አለህ መልእት ቢያስተላልፉም ባይደን ግን በቻይና ላይ የሚገደረውን አለምአቀፍ ተጽእኖ እንደሚመሩ ገልጸው ነበር፡፡ የባይደን አስተዳደር በቻይና ላይ ያለው ፖሊሲ እንዳልቀየረና ጫና ማሰደሩን እንደሚቀጥል ግልጽ አድርጓል፡፡