አሜሪካ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ሃገሪቱን ቅርቃር ውስጥ በከተተው የምርጫ ጉዳይ ላይ እንዲስማሙ አሳሰበች
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ለምርጫው ጉዳይ እልባት ለመስጠት የተጀመረው ውይይት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል
ፖለቲከኞቹ ከፖለቲካው ሊገኝ የሚችለውን ትርፍ በመተው ህዝቡ የሚሻውን ከመካከላቸው እንዲመርጥ ፍላጎቱን ሊያስጠብቁለት እንደሚገባም አሳስባለች
የሶማሊያ ፖለቲከኞች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በንግግር እንዲፈቱ ዓለም አቀፍ ጥሪ ቀረበ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ ተልዕኮ ያላቸው የአፍሪካ ህብረትን፣ የአውሮፓ ህብረትንና የመንግስታቱ ድርጅትን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሃገራት ፖለቲከኞቹ ከአሁን ቀደም በደረሱበት ስምምነት መሰረት ምርጫው በቶሎ ሊካሄድ በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንዲመክሩ ባወጡት ጥምር መግለጫ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተቋማቱ በማዕከላዊ ሶማሊያ በሚገኘው ጋልሙዱግ ግዛት ዱሳማሬብ ከተማ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ሂደት መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን በማስታወስም እስካሁን ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማት እንደሚቻል በማሰብ መነጋገሩ እንዲቀጥልም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
በተረጋጋ እና ገንቢ በሆኑ መንገዶች የሚካሄድ ውይይትን እንደሚደግፉም ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ተቋማቱ ከፊል ምርጫን ጨምሮ ስምምነት ባልተደረሰበት ሁኔታ የሚፈጸሙ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን እንደማይደግፉ አስምረውበታል፡፡
የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆን ጨምሮ የሃገሪቱ ህግ አውጪ አካል የስልጣን ዘመን ዛሬ እ.ኤ.አ የካቲት 8 ነው የሚያበቃው፡፡
የዛሬ ዓመት የተራዘመው ምርጫ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ በወርሃ ጥር እና የካቲት ግድም እንደሚካሄድ ቢጠበቅም በምርጫው አካሄድ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በፕሬዝዳንቱ እና በክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መካከል ስምምነት ላይ ሊደረስ ባለመቻሉ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶችም አልተጀመሩም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን ያበቃው፡፡
ይህን ተከትሎም ተቃዋሚዎች ፋርማጆ ከዛሬ ጀምሮ ህጋዊ ስልጣን እንደሌላቸው በማሳወቅ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡
ከፕሬዝዳንቱ ጋር በምርጫ ጉዳይ ሲደራደሩ የነበሩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም ቢሆኑ ከአሁን በኋላ የፋርማጆን ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከ5ቱ የሃገሪቱ ክልላዊ መስተዳድሮች የሁለቱ መሪዎች ማለትም የፑንትላንድ እና የጁባላንድ መሪዎች ይህንኑ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡
መሪዎቹ ይህን ያሉት በዱሳማሬብ ሲያካሂዱት በነበረው ውይይት ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው ነው፡፡
ይህ ሃገሪቱን ለከፋ ፖለቲካዊ ኪሳራ እንዳይዳርጋት እና ለእነ አል አሸባብ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ተሰግቷል፡፡
አሜሪካም ስጋቷን ገልጻለች፡፡ ሞቃዲሾ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩልም ተመሳሳይ መግለጫንም አውጥታለች፡፡
በመግለጫው የፋርማጆ መንግስት ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተወያይቶ የሃገሪቱን የወደፊት እጣፋንታ ቅርቃር ውስጥ በከተተው ጉዳይ ላይ እንዲስማማ እና ምርጫው በአስቸኳይ እንዲደረግ አሳስባለች፡፡
ባለፈው ዓመት በገጠመው ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት አል ሸባብን በመዋጋት እና በሌሎችም የጸጥታ እና ደህንነት፣ የምግብ ዋስትና እና ተያያዥ ተግባራት የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡
በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ዶናልድ ያማሞቶ የገጠመውን ችግር እንዲፈታ ሃገራቸው ያላትን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
“የውዥንብሩ መፈታት ለሃገሪቱ የወደፊት እጣ ፋንታ ወሳኝ ነው”ም ነው ያለችው አሜሪካ፡፡
የፌዴራል እና የክልል መንግስታቱ ለማትረፍ የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ጥቅም በመተው ህዝቡ የሚሻውን ከመካከላቸው እንዲመርጥ ፍላጎቱን የማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጻለች፡፡
ለቀዳሚ ጉዳዮች እልባት ለመስጠት እና የምርጫ ጣጣዎችን ለመጨረስ ጊዜው አሁን ነውም ብላለች፡፡